ወጣቶች የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች ለፈጠራ ስራ እንደ ምቹ እድል መጠቀም አለባቸው - በፈጠራ ስራ የተሰማሩ ወጣቶች

189
አዲስ አበባ መስከረም 19/2011 ወጣቶች በየአካባቢያቸው የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች መፍትሄ በመፈለግ ለፈጠራ ስራ እንደ ምቹ እድል መጠቀም  እንዳለባቸው በፈጠራ ስራ የተሰማሩ ወጣቶች ተናገሩ።  በርካታ ኢትዮጵያዊያን በእለት ከእለት ኑሯቸው በቀላሉ ሊፈቱ በሚችሉ ችግሮች ውስጥ ያልፋሉ። ኢትዮጵያ እንደአገር የሚያጋጥሟትን ችግሮች መፍታት በሚያስችሉ የፈጠራ ስራዎች ላይ በስፋት የሚሳተፉ ወጣቶችን በማፍራት ረገድ ብዙ እንዳልተጓዘች ይገለጻል። በፈጠራ ስራ ችግር ፈቺ ግኝቶች ያሉዋቸው ወጣቶችም ቢሆኑ ስራዎቻቸውን ወደ ገበያ የሚቀይሩበት ሁኔታዎች ፈታኝ እንደሆኑባቸው በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ከሰሞኑን በአዲስ አበባ የወጣቶቸን ከባቢያዊ የፈጠራ ክህሎት የሚያበረታታና በአሜሪካን ኤምባሲ ድጋፍ የተዘጋጀ የወጣቶች የስራ ፈጠራ ወድድር ተካሂዷል፤ ኤምባሲው ወጣቶች ስራዎቻቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወቃል። ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው ስራ ፈጣሪ ወጣቶች እንደሚሉት፤ ወጣቶች  የሚገጥማቸውን  ችግሮች በመፍታት ወደ መፍትሄ መቀየር እንዳለባቸው ያስዳሉ፡፡ የሚገጥሙን ችግሮችን በመለየት መፍትሄ  ላይ ትኩረት ማድረግ ወደ ስኬት ይወስዳል የሚለው በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪና "ስማርት ኢሪጌሽን" የተባለ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂ ፈጣሪ ወጣት ሄኖክ አዲስ ነው፡፡ "ችግሮችን ችላ ብሎ ከማለፍ ይልቅ ለማቃለል ምን ባደርግ ይሻላል ብለን መጠየቅ አለብን" ያለው ደግሞ ከጓደኛው ጋር ሆኖ በራሱ የሚንቀሳቀስ ዘመናዊ ማረሻ ፈጣሪና በመቀሌ ከተማ የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ወጣት ናታን ገብረህይወት ነው። ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በባዮ ቴክኖሎጂ የተመረቀውና ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ኦክስጅንን ለህሙማን መጥኖ የሚሰጥ ማሽን የፈጠረው ወጣት ዮናስ ገብረወልድ እንደሚለው  ተመራቂ ተማሪዎች ከሰራ ቅጥር ባለፈ ሁሌም አዲስ ነገር ይዘው ምጣት አለባቸው፡፡  "ፈጠራ" ማለት አዳዲስ ነገርን ብቻ ይዞ መምጣት አለመሆኑን የሚናገረው ወጣት ዮናስ፤  የተሰሩ ፈጠራዎችን ለብዙሃኑ በሚጠቅም መልኩ መሻሻልም ሌላው አማራጭ መሆኑን ይናገራል።  የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ኤፍራህ አሊ በበኩላቸው፤ ሚንስቴሩ ወጣቶች በስፋት በቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ በቡራዩ የፈጠራ ክህሎት ትምህርት ቤት እያስገነባ ነው። ይህም የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ህጻናት ወደ ኢንኩቤሽን ማዕከል ገብትው ፈጠራቸውን እንዲያዳብሩ ለማገዝ ማለሙን  በመግለጽ።  ኢትዮጵያ ከምትፈልገው ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች አኳያ የተሰሩት ስራዎች በቂ አለመሆናቸውን ገለጸው፤ ሚንስቴሩ ህጻናት ከልጅነታቸው ጀምሮ  የፈጠራ ስራን ባህል አድርገው እንዲያድጉ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም