ህወሃት የፖለቲካ መስመሩ ልማታዊ ዴሞክራሲ ሆኖ እንደሚቀጥል አስታወቀ

145
መቀሌ መስከረም 19/2011 የአርሶ አደሩንና የደሃውን የከተማ ነዋሪ ህይወት ከመሰረቱ ሳይቀየር መስመሩን እንደማይለውጥ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ህወሃት አስታወቀ። ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ ባለፉት አራት ቀናት የተወያየባቸውንና የደረሰባቸውን ድምዳሜዎች በማስመልከት የጉባኤው ፕሬዝደየም አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ በሰጡት መግልጫ እንዳሉት ጉባኤው ዓለም አቀፋዊ፣አገራዊና ክልላዊ  ሁኔታዎች ላይ ተወያይቷል። ህወሓት ማህበራዊ መሰረቱ አርሶ አደሩ፣ድሀው የከተማ ነዋሪና ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ገቢ የሌለው የማህበረሰብ ክፍል መሆኑን ተናግረው ባለፉት አመታት በተካሔዱ የልማት ስራዎች ውጤት ቢኖርም የህወሃትን የሃይል አሰላለፍ የሚያስቀይር መዋቅራዊ ለውጥ እንደሌለ ተናግረዋል። "ህወሓት የሚከተለው የፖለቲካ መስመር ልማታዊና ዴሞክራሲ ሆኖ ይቀጥላል" ያሉት አቶ ጌታቸው ይህ ማለት ግን የሚፈተሹ ፖሊሲዎች ፣ ስትራተጂዎችና አፈጻጸሞች አይኖሩም ማለት እንዳልሆነ አስታውቀዋል። በ13ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ሌላው ከታዩ ጉዳዮች መካከል በክልሉ ዴሞክራታይዜሽንን የማስፋት ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የመንግስትና የፓርቲ ስራ ሳይቀላቀል ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ መመቻቸቱን ጠቁመው ህዝባዊና ሲቪክ ማህበራትም ከፖለቲካ ተጽዕኖ በመላቀቅ በአባሎቻቸው ፍላጎት መሰረት ዴሞክራሲን የማስፋት ስራ እንዲሰሩ አቋም መያዙን ገልጸዋል፡፡ የአከባቢውን ጸጋ መሰረት ያደረጉ የመንግስት ተቋማትን ዳግም የማደራጀት ስራ እንዲኖር የጉባኤው ተሰታፊ ድምዳሜ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡ ህወሓት በ12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎችና አፈጻጸማቸውን በመገምገም በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡ ህወሓት ዓለም አቀፋዊ፣ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎችን ከመገምገሙም በተጨማሪ የጀመረው የጥልቅ ተሀድሶ አሁን ያለበትን ደረጃ እንደፈተሸ ተናግረዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በዛሬ ውሏቸው በድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት ላይ ውይይት እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። "13ኛው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ ነገ በሚኖረው የማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ድርጅቱ ባስቀመጠው የመተካካት መርህ መሰረት አዳዲስ ምሁራንና ሴቶች ወደ ማእከላዊ ኮሚቴ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም