በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ገጽታ ሙሉ በሙሉ መቀየር ይቻላል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

150
አዲስ አበባ ግንቦት 12/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ "በዚሕ ሕብረት ከቀጠልን በሚመጡት አስር ዓመታት ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ሁኔታ መቶ በመቶ መቀየር" ይቻላል ሲሉ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በሚሌኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የልህቀት ግንባታ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለውን አንድነትና አገራዊ ስሜት አድንቀዋል። ዶክተር አብይ "የውጪ አገር ዳያስፖራዎች  እውቀትና ሀብት ይዘው ቢመለሱ፤ በሚመጡት አስር ዓመታት ኢትዮጰያን አሁን ካለችበት ሁኔታ መቶ በመቶ መቀየር ይቻላል" ሲሉ አብራርተዋል። ዜጎች ከአገር የወጡትበችግርና በመገፋት ሊሆን እንደሚችል ያወሱት ዶክተር አብይ በስደት የሚኖሩ ዜጎች ለአገር ያላቸው ፍቅር ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል። 'ዳያስፖራዎች ቤት ገንብተን፣ መኪና ገዝተንና አስፓልት አንጥፈን ለመቀበል ዛሬ ላይ በአገሪቱ አቅም ባይቻልም እንኳን እንደ ዜጋ የምትቆጠሩበት፣ ፍቅርና ክብር ያላቸው ሕዝቦች እጃቸውን ዘርግተው ይቀበሏችኋል' በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ተመልሰው በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በልምድ፣ በእውቀት እንዲያገለግሉ  ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር ግንባታ ያላቸውን ሚናና ከመንግስት ጋር መስራት ስለሚጠበቅባቸው አገራዊ ተግባር ተናግረዋል። 'አገርን መውደድ፣ ለሀገር በጎ ማሰብ፣ ለዚያም መታገል፣ ለሁሉም ዜጎች የሚገባና የሚያስፈልግ ቢሆንም ከእናንተ የሚጠበቀው ሐሳብ በማፍለቅ ኢትዮጵያን በሐሳብ መርዳት ነው' ሲሉ አስገንዝበዋል። 'በሰለጠነ መንገድ ምርጫ ስናካሂድ፣ ቢሮ የምንቀያየር፣ ሐሳብ የምንቀያየርና የማንጠላለፍ መሆን አለብን' ብለዋል። አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ለማስቀጠል ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራትና ሐሳብ መቀያየር አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል። ሁሉም ወገን ጸብ፣ ጥላቻና ቂምን ትቶ ይቅር ተባብሎ መመለስ አስፈላጊ እንደሆነም አብራርተዋል። 'ይቅርታና ፍቅር የማሸነፊያ መንገድ መሆኑን በጽኑ አምኖ መስራት ያስፈልጋል ያሉት' ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ማሸነፍ የምትፈልጉ ከሆነ በፍቅርና በይቅርታ እናሸንፍ" በማለት በንግግራቸው አሳስበዋል። በመጨረሻም ዶክተር አብይ 'አሁን በተጀመረው አንድነት መሄድ ከቻልን ኢትዮጵያ ትልቅና የተከበረች አገር እንደምትሆን አትጠራጠሩ' በማለት ተስፋቸውን አንጸባርቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም