ለተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ

267

(በሙሴ መለስ)

በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሔደ ያለው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 60 ጨዋታዎች ተደርገው የግማሽ ፍጻሜ ላይ ደርሷል።

የዓለም ዋንጫ አሸናፊ መሆን ትልቁ የእግር ኳስ ክብር እና ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል።

በዓለም ዋንጫው የሚሳተፉ አገራት እና ተጫዋቾች ሻምፒዮን ተብለው መጠራትም ትልቁ ሕልማቸው ነው።

ሁሉም በዓለም ዋንጫ የሚሳተፍ ተጫዋች በውድድሩ አይን ውስጥ የሚያስገባውን ብቃት በማሳየትና አገሩን ውጤታማ በማድረግ ስሙ በታሪክ ድርሳን እንዲጻፍለት መፈለጉም ሃቅ ነው።

በዓለም ዋንጫ የመጫወትና የማሸነፍ ክብር ለተሳታፊዎቹ ከምንም ጋር የሚነጻጸር ባይሆንም በውድድሩ የሚገኘው የገንዘብ ሽልማትም ቸል የሚባል አይደለም።

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ክብረ ወሰን የሆነ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ሽልማት ፈንድ ማዘጋጀቱን ገልጿል።

ፈንዱ ለአጠቃላይ ሽልማት፣ለክለቦች ተጠቃሚነት ፕሮግራም፣ለክለቦች የጥበቃና የዋስትና ክፍያ እንዲሁም ለአገራት ዝግጅት ክፍያ ይውላል።

አጠቃላይ ሽልማቱ ከአራት ዓመት በፊት ሩሲያ ባሰናዳችው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከተበረከተው 791 ሚሊዮን ዶላር የ29 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው።

ጭማሪው የመጣው ፊፋ እ.አ.አ 2019 እስከ 2022 ከተፈራረማቸው የቴሌቪዥን ስርጭት እና የስፖንሰር ስምምነቶች ነው።

ፊፋ በተጠቀሰው አራት ዓመት ውስጥ ባዘጋጃቸው ትልቅ ውድድሮች ያገኛቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና ኦንላይን መሳራጨት መብቶች ሽያጭ የሽልማት ፈንዱን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮለታል። 

ፊፋ እ.አ.አ 1982 ስፔን ባዘጋጀችው 12ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለውድድሩ ያዘጋጀው የገንዘብ ሽልማት መጠን 20 ሚሊዮን ዶላር ነበር።

የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ አሸናፊ 42 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኝም አመልክቷል።

ይህም ፈረንሳይ ከአራት ዓመት በፊት በሩሲያ አስተናጋጅነት በተካሄደው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አሸናፊ ስትሆን ካገኘችው የገንዘብ ሽልማት የአራት ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አለው።

እ.አ.አ በ1982 ስፔን ባዘጋጀችው 12ኛው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ጣልያን በወቅቱ ያገኘችው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ነበር።

በዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ደርሶ የተሸነፈው አገር 30 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሶስተኛና አራተኛ የወጡት አገራት በቅደም ተከተል 27 እና 25 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኙ ይሆናል።

በዓለም ዋንጫው ግማሽ ፍጻሜ የገቡት ሞሮኮ፣ክሮሺያ፣አርጀንቲና እና ፈረንሳይ እያንዳንዳቸው 25 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ።

በውጤታቸው መሰረት በዓለም ዋንጫው ከ5 እስከ 8 የሚወጡ አገራት እያንዳንዳቸው በተመሳሳይ 17 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከ9 እስከ 16 ያጠናቀቁት ደግሞ እያንዳንዳቸው በተመሳሳይ 13 ሚሊዮን ዶላር ይሰጣቸዋል።

ከምድባቸው ያላለፉ አገራት እያንዳንዳቸው 9 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኙ ፊፋ ገልጿል።

በተጨማሪም አገራቱ በዓለም ዋንጫው በመሳተፋቸው ብቻ እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ።

ፊፋ ከዓለም ዋንጫው በፊት ለ32ቱ አገራት የመነሻ የውድድር ዝግጅት ወጪ መሸፈኛ የሚሆን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር አከፋፍሏል።

በዓለም ዋንጫው ፊፋ የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት እ.አ.አ 1982 ስፔን ካዘጋጀችው 12ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አንስቶ ቀስ በቀስ እያደገ መጥቷል።

በ12ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ የበላይ ጠባቂው አካል 20 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ብቻ ነበር ለ24 ተሳታፊ አገራት ያከፋፈለው።

እ.አ.አ በ2010 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 19ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 420 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ብራዚል እ.አ.አ በ2014 ባዘጋጀችው 20ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 576 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለአገራት ተሰጥቷል።

ከአራት ዓመት በፊት ሩሲያ ባዘጋጀችው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 791 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለተሳታፊ አገራት ተበርክቷል።

ፊፋ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ያዘጋጀው ሽልማት አንድ ቢሊዮን ዶላር ደፍኖ ክብረ ወሰን ሰብሯል።

ይህም አገራቱ በዓለም ዋንጫ በርከት ያለ ገንዘብ የሚያገኙበት አድርጎታል።

ፊፋ ገንዘቡን ለአገራቱ ብሔራዊ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች የሚያከፋፍል ሲሆን በዓለም ዋንጫው ለተሳተፉ ተጫዋቾች ገንዘብ የመስጠት ውሳኔ ግን የፌዴሬሽኖቹ እንደሚሆን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም