ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ በ18 አዳዲስ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ይቀበላል

102
ባህር ዳር መስከረም 19/2011 ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2011 የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ፣ በ2ኛ እና በዶክትሬት ዲግሪ በሚከፍታቸው 18 አዳዲስ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበልም አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል። የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ተቋሙ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን በመክፈት ሃገራዊ እድገቱን በእውቀት ለማገዝ እየሰራ ነው። በተያዘው የትምህርት ዘመንም ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 12 የሁለተኛ ዲግሪና አራት የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ  250 ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል። ዶክተር እሰይ እንዳሉት ህግ፣ መሬት አስተዳደር፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ትምህርት፣ ፖለቲካል ሳይንስና የመሳሰሉት የትምህርት መስኮች አዲስ የሚከፈቱባቸው ናቸው። "የተሳካ የመማር ማስተማር ተግባር ለማካሄድም ቀደም ብሎ የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ መደረጉንና የመምህራን ቅጥርም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል" ብለዋል። የኒቨርሲቲው በአፋን ኦሮሞ ትምህርትም በዚህ ዓመት አጋማሽ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ ሥራ ማካሄዱንና የመምህራን ቅጥር እየፈጸመ መሆኑን ዶክተር እሰይ አስታውቀዋል። ተቋሙ በህክምናው ዘርፍ የተሻለ እውቅት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ "የተሻለ የማስተማርም ሆነ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አዲስ የማስተማሪያ ሆስፒታል ገንብቶ የ170 መምህራንን በመቅጠር ላይ ነው" ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው በመደባኛው የትምህርት መርሀግብር ብቻ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል። በተለይም እንደ ሃገርም ሆነ እንደ ዩኒቨርሲቲ እየወረደ የመጣውን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የተሻለ አቅም ያላቸውን መምህራን በመመደብ፣ ቤተ ሙከራዎችንና ቤተ መጻህፍትን በማደረጀት ጥራትን ለማምጣት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል። ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊትም አጠቃላይ የጥራት መለኪያ ፈተና እንዲወስዱም እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛውና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓመታዊ የተማሪ የቅበላ አቅሙ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም