ለማይጨው ከተማ የተዘጋጀው አዲስ የእድገት ማስተር ፕላን ሥራ ላይ ሊውል ነው

66
ማይጨው መስከረም 19/2011 ለማይጨው ከተማ የተዘጋጀው አዲስ የእድገት ማስተር ፕላን ከተያዘው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ሥራ ላይ እንደሚውል ተጠቆመ። ማስተር ፕላኑ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በመደበው 3 ሚሊዮን ብር ተዘጋጅቶ መጠናቀቁም ተመልክቷል። የከተማው ከንቲባ አቶ አታክልቲ ፀጋይ ለኢዜአ ዛሬ እንደገለጹት አዲሱ የከተማው የእድገት ማስተር ፕላን ሲዘጋጅ የነበረው ከ2010 መስከረም ወር ጀምሮ ነው። ማስተር ፕላኑ በዘርፉ ባለሙያዎች ተገምግሞና በከተማው ነዋሪዎች የተሰጡትን የማሻሻያ ሃሳቦችን በማካተት ለከተማው አስተዳደር ምክር ቤት በመጽደቁ በቅርቡም ሥራ ላይ እንደሚውል አመልክተዋል። እንደ አቶ አታክልቲ ገለጻ አዲሱ የከተማው ማስተር ፕላን ከተጀመረው የ2011 ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ነባሩ ማስተር ፕላን ሲዘጋጅ የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት በሚፈለገው መጠን ያላካተተና ሥራ ላይ ሲውልም የከተማውን እድገት የሚመጥን ሆኖ ባለመገኘቱ አዲስ ማስተር ፕላን ማስፈለጉን ከንቲባው አስረድተዋል። "በተለይ ነባሩ ማስተር ፕላን 43 በመቶ የሚሆነውን የከተማውን ቦታ ለአረንጓዴ ልማት በማካተት የመኖሪያና የንግድ ሕንጻዎችን ለመገንባት ይከለክል ስለነበር በአዲስ ማስተር ፕላን እንዲተካ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል" ብለዋል። በአዲሱ ማስተር ፕላን የከተማዋ የአረንጓዴ ልማት ክልል ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲል የተደረገ ሲሆን ይህም ህዝቡ የመሬት ይዞታውን ለማልማት ሲያቀርበው ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል። ማስተር ፕላኑ አሁን ያለውን 1 ሺህ 466 ሄክታር የከተማው የቆዳ ስፋት ወደ 2 ሺህ 300 ሄክታር የሚያሳድግና ለመኖሪያነት ምቹ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን አቶ አታክልቲ ተናግረዋል፡፡ ይህም ነዋሪዎች የመሬት ይዞታቸውን በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት። ነባሩ ማስተር ፕላን ህዝቡ የመሬት ይዞታውን እንዳያለማ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ሙላው ማርቆስ ናቸው፡፡ አቶ መሀሪ ታደለ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው አዲሱ ማስተር ፕላን የጠባብ መንገዶችን ደረጃ ለማሳደግና አዳዲስ መንገዶችን ለመክፈት የሚያስችል በመሆኑ ለከተማው እድገት ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡ ከእዚህ በተጨማሪ የውሃ መቀልበሻ ካናሎች የሚሰሩበትን አካባቢ ለይቶ ስለሚያስቀምጥ በክረምት ወራት ከጎርፍ አደጋ እንደሚታደጋቸው ነው ያስረዱት።  ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አብርሃ ስዩም በበኩላቸው "አዲሱ ማስተር ፕላን በከተማው በጥቂት ተቋማት የተያዙትን ሰፋፊ መሬቶች ለማህበራዊ አገልግሎት ግንባታ እንዲውሉ የሚያደርግ በመሆኑ የከተማውን የእድገት ማነቆ ያቃልላል የሚል እምነት አለኝ" ብለዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም