ፈጠራችንን ተጠቅመን የዘይት ምርት ለገበያ ማቅረብ ጀምረናል...በማይጨው ከተማ በማህበር የተደራጁ ምሩቃን

200
ማይጨው መስከረም 18/2011 በማይጨው ከተማ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በማህበር የተደራጁ ስምንት ወጣቶች የራሳቸውን ፈጠራ በመጠቀም በሰሩት የምግብ ዘይት መጭመቂ ታግዘው ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን አስታወቁ ። የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት መሀሪ ገብረእግዝአብሄር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፀው አባላቱ የመንግስት ስራ ከመጠበቅ ይልቅ በአካባቢው አዋጭ የገበያ ጥናት በማድረግ ወደ ሥራ ገብተዋል ። "ፈጠራችን በመጠቀም የሰራነው የዘይት መጭመቂያ ማሽን በውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን በመተካት በቅርቡ ማምረት ጀምሯል " ብሏል። በሰሩት የዘይት መጭመቂያ ማሽን ታግዘው ባለ አንድና ሦስት ሊትር የታሸገ የዘይት ምርት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውንም ተናግሯል ። "መጭመቂያ ማሽኑ በቀን ከ6 እስከ 8 ሺህ ሊትር ዘይት የማምረት አቅም አለው" ያለው ወጣት መሀሪ ከኑግ፣ ሰሊጥና ሌሎች የቅባት እህሎች ለሚያመርቱት ዘይት ከተስማሚነትና ምዝና ኤጀንሲ የጥራት ማረጋገጫ ሰርትፊኬት ማግኘታቸውን ተናግሯል ። የማህበሩ አባላት ባቀረቡት የፕሮጀክት ዕቅድ መሰረት መንግስት ከመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድርና የማምረቻ ስፍራ ድጋፍ ታግዘው ወደ ስራ መግባታቸውንም ወጣትመሀሪ አስታውሷል ። የማህበሩ ምክትል ሊቀመንበርና በመካኒካል ኢንጂነሪንግ የተመረቀው ወጣት ክብሮም ሀጎስ  በማህበሩ የሚመረተውን ዘይት ከአካባቢው በተጨማሪ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል ። ያቋቋሙት የዘይት ማምረቻ ለተጨማሪ ሰባት ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥሯል ። የማይጨው ከተማ አስተዳደር የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ካሳ ወጣቶቹ በተሰማሩበት የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የእውቅና ምስክር ወረቀት  የተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል ። ለማህበሩ አባት መንግስት ከመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ የገንዘብ ብድር በተጨማሪ ለማምረቻ የሚሆን ስፍራ በአስተዳደሩ በኩል ድጋፍ የተደርጎላቸዋል ። በከተማው በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማሩት  አቶ ንጉስ መረሳ በበኩላቸው ከወጣቶቹ ተረክበው ለገበያ የሚያቀርቡት ዘይት ከአስተሻሸጉ ጀምሮ በንፅህናውና በዋጋው በደንበኞቻቸው ዘንድ ተፈላጊነት እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል። "ማህበሩ የሚያመርተው ዘይት የማይረጋና  በጣዕሙ የተሻለ  ሆኖ አግኝቸዋለሁ" ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ለምለም ኃይሉ የተባሉ የማይጨው ከተማ ነዋሪ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም