በአማራ ክልል የስድስት ፋብሪካዎች ግንባታ ሊጀመር ነው

52
ባህርዳር መስከረም 18/2011 የአባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ የስድስት ፋብሪካዎች ግንባታ ስራ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደምስ ተሻገር ለኢዜአ እንደገለጹት ግንባታቸው በዚህ ዓመት የሚጀመረው የሲሚንቶ፣ የጨርቃጨርቅና ጋርመንት፣ የእንጨትና ብረታብረት ፋብሪካዎች ናቸው። የክልሉ መንግስት፣ የልማት ድርጅቶችና ባለሃብቶች በጋራ ባቋቋሙት አክሲዮን ማህበር ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገነቡ ፋብሪካዎች የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን አውስተዋል። ለፋብሪካዎቹ ግንባታም 193 ሄክታር መሬት ከየከተማ አስተዳደሮች ተረክቦ ለልማት ተነሺዎች ካሳ የመክፈልና የመብራት፣ የውሃ፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የማሟላት ስራ እየተካሔደ ነው። ከሚገነቡት ፋብሪካዎች መካከልም የክልሉ መንግስት ቀደም ብሎ በጎንደር ከተማ ያስገነባቸው ሶስት ሸዶችን ተረክቦ የጋርመንት ስራ ለመጀመር ማሽነሪዎችን ከውጭ እያጓጓዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል። “ለስራው የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችና ሰራተኞችን ለመቅጠርም ምልመላና መረጣ እየተካሄደ ሲሆን የማሽነሪ ተከላ ስራው ተጠናቆ በመጭው የካቲት 2011 ዓ.ም የማምረት ስራ ይጀምራል”ብለዋል። ለስሚንቶና ለብረታ ብረት ፋብሪካዎች ዓለም አቀፍ አማካሪዎች ቀደም ሲል መቀጠራቸውን ገልጸው ለሌሎች ፋብሪካዎችም አማካሪዎችን ለመቅጠር በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይ በደጀን ወረዳ ለሚገነባው የሲሚንቶ ፋብሪካ ዓለም ጨረታውን ያሸነፈው አካል በመለየቱ እስከ መጭው ህዳር ወር የግንባታ ስራውን እንደሚጀመር ገልጸዋል። ባህርዳር ላይ የሚገነባው የብረታ ብረት ፋብሪካም ጥናቱ ተጠናቆ ከ20 በላይ አለምአቀፍ ድርጅቶች የጨረታ ሰነዱን በመውሰዳቸው በቅርቡ አሸናፊው ተለይቶ ወደ ግንባታ እንደሚገባ አመልክተዋል። ሶስት የኤምዲኤፍ የእንጨት ፋብሪካዎችን ጨምሮ የጨርቃጨርቅ፣ የሲሚንቶና፣ የብረታ ብረት ፋብሪካዎች እስከያዝነው ዓመት አጋማሽ ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው። “አክሲዮን ማህበሩ መቋቋም ያስፈለገውም ባለሃብቱና የክልሉ መንግስት፣ እንዲሁም ባለሃብቱ እርስ በእርሱ ጠንካራ አንድነት ፈጥሮ የክልሉን ልማት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ነው” ብለዋል። በአራት ዓመት ውስጥ ሁሉም ፋብሪካዎች ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቁ ከአራት ሺህ ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ታውቋል። ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት እንዲገነቡም የስራ አመራር ቦርዱና የክልሉ መንግስት በጋራ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉም አስረድተዋል። የስሚንቶ ፋብሪካው በዓመት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል፣ የብረት ፋብሪካው በቀን 300 ሺህ ቶን ብረት፣ የእንጨት ፋብሪካዎቹ ደግሞ 180 ሺህ ሜትሪክ ቶን በቀን ማምረት እንደሚችሉ ለአብነት ጠቅሰዋል። የአባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር የተመሰረተው በአራት ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል ሲሆን እስካሁንም ከአባላቱ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰቡን ጠቁመዋል። አክሲዮን ማህበሩ በክልሉና ከክልሉ ውጭ የሚገኙ ከ250 በላይ ባለሃብቶችና የልማት ድርጅቶችን በአባልነት አሰባስቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም