የነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ወደ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደረጃ ማደጉ ተጠቃሚ አድርጎናል...ተገልጋዮች

76
ነቀምት መስከረም 18/2011 የነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ወደ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በማደጉ የተሟላ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ተገልጋዮች ገለጹ። በነቀምቴ ከተማ የቀበሌ 02 ነዋሪ ወይዘሮ አበባዬ ደበላ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት እሳቸውን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪ የልብ፣ የካንሰርና የኩላሊት ሕክምና ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ይገደዱ ነበር። በአሁኑ ወቅት የነቀምቴ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እነዚህን የሕክምና አገልግሎቶች መስጠት በመጀመሩ በአቅራቢያቸው የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ይህም የትራንስፖርት፣ የምግብና የመኝታ ወጪያቸውን ማስቀረቱን ነው የገለጹት። በምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ገሊላ ከተማ ቀበሌ 01 የሚኖሩት አቶ ገመዳ ፉፋ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ለከባድ ቀዶ ሕክምና አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ እና ጳውሎስ ሆስፒታሎች በቅብብሎሽ ተልከው ስለሚታከሙ ለከፍተኛ ወጪ ሲዳረጉ ቆይተዋል። አሁን ግን በከተማዋ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመኖሩ በዚህ በኩል ያለባቸው ችግር መቃለሉን ተናግረዋል። "በተለይ ለቀዶ ጥገና የሚያገለግሉ የህክምና ቁሳቁስ፣ መድሃኒትና ሌሎችም መርጃ መሳሪያዎች በተሟሉ መልኩ በሆስፒታሉ በመኖሩ የተሟላ አገልግሎት እያገኘን ነው "ብለዋል። ሆስፒታሉ ደረጃውን ማሳደጉ በህሙማን  ላይ ይደርስ የነበረውን  እንግልትና ሞት ያስቀራል የሚሉት ደግሞ ሌላዋ የገሊላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አያንቱ ቱፋ ናቸው። የነቀምቴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ታሪኩ ታደሰ ተቋሙ ወደ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደረጃ ያደገው ከመስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል። በሆስፒታሉ ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና፣ ሲቲስካን፣ የዓይን፣ የጥርስና ሌሎችንም የጠና አገልግሎቶች እንደሚሰጡ አመልክተዋል። ዶክተር ታሪኩ እንደሚሉት ሆስፒታሉ ወደ ስፔሻላይዝድ  ደረጃ ከማደጉ ጋር ተያይዞ ከ7 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለእናቶችና ለሕፃናት አገልግሎት የሚሰጡ ባለ ሶስት ኮምፕሌክስ ሕንፃ ለማስገንባት እየተንቀሳቀሰ ነው። በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ስፍራ ላይ የሚገነባው ኮምፕሌክስ 100 የህሙማን መኝታ ክፍሎች ይኖሪታል። በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ በተለያየ ሙያ ስፔሻሊስት የሆኑ ዘጠኝ ሐኪሞችን ጨምሮ 400 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች ይገኛሉ። የነቀምቴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በምዕራብ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ሰባት የኦሮሚያ ዞኖች እንዲሁም በጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ክልሎች ለሚኖሩ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም