የብልጽግና ፓርቲ በጠንካራ አመራር የነበሩ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በርካታ ስኬት አስመዝግቧል - የፓርቲው የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት

152

ሐዋሳ ኢዜአ ታህሳስ 1 ቀን 2015፦የብልጽግና ፓርቲ በጠንካራ አመራር ባስቀመጠው አቅጣጫ የነበሩ ሀገራዊ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በርካታ ስኬት አስመዝግቧል ሲሉ የፓርቲው የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።

የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ከለውጡ በኋላ ይሳካሉ ተብለው የማይታሰቡ በርካታ የልማትና የዴሞክራሲ ውጥኖችን በማሳካት የተደቀኑ ፈተናዎችን መቀልበስ መቻሉን ገልጸዋል።

በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ  ባለው የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች መካከል የብልጽግና ማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብርሃም አለኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከተሰራ የላቀ ድል ማስመዝገብ እንደሚቻል ታይቷል።

ከሰላምና ደህንነት አንጻር እንቅፋቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ የሚያስችል ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የደህንነት ስጋት በአጭር ጊዜ መቀረፍ አለበት የሚል አቅጣጫ በፓርቲው መቀመጡን ገልጸው፤ ሰላምን ለማረጋገጥ ጥረትና ትጋት መደረግ እንዳለበት ፓርቲያችን አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

ሌላዋ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሎሚ በዶ ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን በማለፍ ድል እያስመዘገበች እንደሆነ ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ያለው አመራር በቁርጠኝነት፣ በፍጹም ታማኝነትና ተነሳሽነት በመስራቱ ለስኬት መብቃቱን ጠቅሰው፤ በተለይ የፓርቲያችን ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሰጡት ቆራጥ አመራር አገራችን ሲገጥሟት የነበሩ ችግሮችን ወደ ዕድል በመቀየር ትላልቅ ድሎች ተገኝተዋል ብለዋል።

እየተሰጠ ባለው አመራር ጠንክረን ከቀጠልን ብዙ ተስፋዎች ከፊታችን አሉ ሲሉም ተናግረዋል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ህዝብን ለማዳመጥና በህዝብ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታትና ብልሹ አሰራሮችን መታገል በተለይም ሌብነት ላይ ግልጽ አቋም በመያዝ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

እንደ የብልጽግና ማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብርሃም አለኸኝ ገለጻ፤ ከለውጡ በፊት ተጀምረው ሲጓተቱ የነበሩ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ስራዎች በፓርቲው አመራር ሰጪነት ተሰርተዋል።

ለአብነትም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በፓርቲው ቆራጥ አመራር ሰጪነት የነበረበት ጫና ሁሉ ተፈትቶ እስከ ሶስተኛ ዙር ድረስ የውሃ ሙሌት መካሄዱንና ሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት መጀመራቸውን አስታውሰዋል።

በተለያዩ ዘርፎች ስኬት እየተመዘገበ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ሎሚ በዶ፤ በማኑፋክቸሪን፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እንዲሁም በቴክኖሎጂ ኢትዮጵያን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ፓርቲው የህዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን በመለየት በየደረጃው ህዝቡን ባሳተፈ አካኋን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በተለይ ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በከተማና በገጠር የህብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፤ የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ የሰራቸውን በርካታ ተግባራት አስታውሰዋል።

የብልጽግና ፓርቲ 1ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት በሐዋሳ ከተማ ትናንት መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም