ብልፅግና ፓርቲ ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

143

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 1 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- ብልፅግና ፓርቲ ከተመሰረተ ወዲህ በርካታ ጉዳዮችን በመናበብና በመቻቻል ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር የጀመረውን ስራ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል በፖርቲው ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኽኝ አስታወቁ።

በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ  ባለው የብልፅግና ፖርቲ አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት አቶ አብርሃም እንደገለጹት፤ ፓርቲው ከተመሰረተ ማግስት ጀምሮ በርካታ ጉዳዮችን በመናበብና በመቻቻል ለመፈጸም ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በዚህም  በርካታ የዴሞክራሲ ተቋማት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት አንዱ የሆነው ምርጫ ቦርድ በአዲስ ሪፎርም ካደረገ በኋላ የተሻለ ደረጃ ላይ ነው ያለው ብለን እናምናለን ብለዋል።

እንደ ብልጽግና ፓርቲ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ነው የተነሳነው ያሉት አቶ አብርሀም፤ ፓርቲው አስቸኳይ ጉባዔ እንዲያደርግ ዴሞክራሲ ተቋሙ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተቀብሎ መፈጸም ለኛ ከዴሞክራሲ ልምምድ አኳያ እንደ ድል ነው የምንቆጥረው ሲሉ ገልጸዋል።

ከአንደኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ በመነሳት ምርጫ ቦርድ እንዲስተካከል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለመፈጸም የወሰድነው ቁርጠኝነት በአጠቃላይ ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።

ፓርቲው ከተመሰረተ ወዲህ በርካታ ጉዳዮችን በመናበብና በመቻቻል ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር የጀመረውን ስራ  አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ይህ ስራ ምርጫ ቦርድም የበለጠ ዴሞክራሲያዊነቱ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ ከማድረግ አኳያ የራሱን አስተዋጾ ያደርጋል ብለዋል።

ጉባኤው በትናንቱ ውሎው በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲካተቱ የቀረቡለትን 10 አባላት ተቀብሎ አፅድቋል።

በዚህም መሰረት የብልፅግና ፖርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሆነው የተካተቱት ጁል ናንጋል ከጋምቤላ፣ ቀበሌ መንገሻ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ መስከረም ደበበ ከኦሮሚያ፣ ታደሰ ገብረ ፃዲቅ፣ አብርሀም አያሌው፣ ዲያቆን ተስፋሁን ባንተያብል፣ ደሳለኝ ጣሰው፣ ወርቁ ኃይለማርያም፣ ዘውዱ ማለደ እና መሐመድ ያሲን ከአማራ ክልል ናቸው።

በማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲካተቱ የተደረገው ምርጫ ቦርድ እንዲስተካከል ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በፖርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 17 ንዑስ አንቀፅ (ሸ) መሰረት የተከናወነ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም