የአላውሃ ወንዝ የብረት ድልድይ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

170

አዲስ አበባ ኢዜአ ታህሳስ 01 ቀን 2015፦በሰሜን ወሎ ዞን ከወልዲያ ወደ ቆቦ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የአላውሃ ወንዝ የብረት ድልድይ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

ቀደም ሲል 102 ሜትር ርዝመት የነበረው ድልድዩ በኮንክሪት ደረጃ በጣልያኖች ተገንብቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ እንደነበርም አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

ጉዳቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ትንንሽ እና መለስተኛ ተሽከርካሪዎች በኮምቦልቻ ዲስትሪክት የተሰራውን ተለዋጭ መንገድ በመጠቀም እና ወንዙን በማቋረጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውም ተጠቅሷል።

የድልድይ ጥገና ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ለሁለት ወራት የተለመደው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ ቆይቷል።

ድልድዩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ጉዳት ከደረሰበት በኋላ 54 ነጥብ 86 ሜትር ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ ተሰርቶለት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የክረምቱን ማየል ተከትሎ ነሐሴ 09/2014 ምሽት ላይ የተከሰተው ድንገተኛ ጎርፍ የድልድዩን ተሸካሚ ምሶሶዎች በማፍረሱ በጊዜያዊነት የተሠራው የብረት ድልድይ ላይ የመውደቅ ስጋት አስከትሎ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የብሪጅ ስትራክቸር ዳይሬክቶሬት እና ኮምቦልቻ ዲስትሪክት ባለፉት ሁለት ወራት አስፈላጊውን የጥገና ቁሳቁስ ወደ ቦታው በማንቀሳቀስ ድልድዩን ሲገነቡ ቆይተዋል።

በአዲስ መልክ የተገነባው የብረት ድልድይ 109.73 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ግንባታውን ለማጠናቀቅ ላለፉት ሁለት ወራት ሌት ከቀን ስራው ሲሰራ እንደቆየ ተመላክቷል።

ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረው ድልድዩ በአሁኑ ወቅት በብረት ድልድይ በመተካት በአዲስ መልኩ ተገንብቶ ከዛሬ ታህሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለትራንስፖርት አገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

የብረት ድልድዩ እስከ 400 ኩንታል ወይም 40 ቶን ድረስ የመሸከም አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እንደተገነባም ተጠቅሷል።

መንግስት በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ጉዳት የደረሰባቸውን የመሰረተ ልማቶች አገልግሎት የማስጀመር ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል።

በሌላ በኩል ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻልም 120 ሜትር ርዝመት ያለው የኮንክሪት ድልድይ ግንባታ ዲዛይን መጠናቀቁንና ስራውን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም