ሞሮኮ በዓለም ዋንጫው የራሷን አዲስ ታሪክ ትሰራ ይሆን?

288

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 1/2015 አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ከአህጉሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት ዛሬ ከፖርቹጋል ጋር ወሳኝ ፍልሚያ ታደርጋለች።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰአት 40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው አል ቱማማ ስታዲየም ይደረጋል።

በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አስደናቂ ግስጋሴ እያደረገች የምትገኘው ሞሮኮ በጥሎ ማለፉ ስፔንን በመለያ ምት 3 ለ 0 በማሸነፍ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍጻሜ ገብታለች።

የአትላስ አንበሶች አንድ እርምጃ ተራምደው በዓለም ዋንጫው ግማሽ ፍጻሜ በመግባት ለአፍሪካ ታሪክ መስራት ከፈለጉ ከፊታቸው የቆመችውን ፖርቹጋልን ማሸነፍ ይጠበቅቸዋል።

ሞሮኮና ፖርቹጋል ቀደም ሲል ለሁለት ጊዜያት እርስ በእርስ የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም ግንኙነታቸው በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ ነው።

እ.አ.አ በ1986 ሜክሲኮ ባሰናዳችው 13ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ስድስት ተገናኝተው ሞሮኮ በአብደራዛቅ ካሂሪ ሁለት ግቦች እንዲሁም አብዱልከሪም ሜሪ ባስቆጠራት አንድ ግብ ፖርቹጋልን 3 ለ 1 አሸንፋለች።

ይሄም የአትላስ አንበሶች በዓለም ዋንጫው ያገኙት የመጀመሪያ ታሪካዊ ድላቸው ሆኖ ተመዘግቧል።

ዲያማንቲኖ ሚራንዳ በወቅቱ ለፖርቹጋል ግቡን ያስቆጠረ ተጫዋች ነበር።

ሁለቱ አገራት በዓለም ዋንጫው ለሁለተኛ ጊዜ የተገናኙት ከ32 ዓመት ቆይታ በኋላ ሩሲያ እ.አ.አ በ2018 ባዘጋጀችው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ነው።

በምድብ ሁለት በተደረገው ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጨዋታው በተጀመረ አራተኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ፖርቹጋል ሞሮኮን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

የ40 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ፋኩንዶ ቴሎ የዛሬ ተጠባቂውን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰአት 60 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው አል በይት ስታዲየም የወቅቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ፈረንሳይ ከእንግሊዝ የሚያደርጉት ጨዋታ በጣም ተጠባቂ ነው።

ሁለቱ የአውሮፓ እግር ኳስ ኃያላን በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

እ.አ.አ በ1966 እንግሊዝ አዘጋጅታ ራሷ በወሰደችው ስምንተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ሮጀር ሀንት ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ሶስቱ አናብስቶች ፈረንሳይን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።

ሁለቱ አገራት ከ16 ዓመታት በኋላ ስፔን እ.አ.አ 1982 ባዘጋጀችው 12ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አራት ተገናኝተው እንግሊዝ በብራያን ሮቢንሰን ሁለት ግቦች እንዲሁም ፖል ማሪነር ባስቆጠራት አንድ ግብ ፈረንሳይን 3 ለ 1 አሸንፋለች።

ጌራርድ ሶላር በወቅቱ ለፈረንሳይ ግቡን ያስቆጠረ ተጫዋች ነበር። ፈረንሳይና እንግሊዝ በአጠቃላይ እስከ አሁን 31 ጊዜ እርስ በእርስ በኳስ ሜዳ ላይ ተገናኝተዋል።

በዚህም እንግሊዝ 17 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ፈረንሳይ ዘጠኝ ጊዜ አሸንፋለች። አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በ31ዱ ጨዋታዎች 108 ግቦች ተቆጥረዋል። እንግሊዝ 69 እንዲሁም ፈረንሳይ 39 ግሎችን አስቆጥረዋል።

የ40 ዓመቱ ብራዚላዊ ዊልተን ሳምፓዮ የዛሬውን የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች ረቡዕ ታህሳስ 5 ቀን 2015 ዓ.ም በአል በይት ስታዲየም የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ትናንት በተደረጉ የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች አርጀንቲና እና ክሮሺያ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም