የአዲስ አበባ ከተማን ጽዳት ለማስጠበቅ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የቁጥጥር ስራውን ነገ በይፋ ይጀምራል

178

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ህዳር 30/2015 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት የከተማዋን ጽዳት ለማስጠበቅ ያቋቋመው ግብረ ኃይል የቁጥጥር ስራውን ነገ በይፋ ይጀምራል።

ግብረ ሀይሉ ከተማውን በሚያቆሽሹ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ  ጽህፈት ቤት የከተማዋን ጽዳት ለማስጠበቅ የሚያስችል ለ3 ወር የሚቆይ የህገ-ወጥ ቆሻሻ መከላከል ግብረሀይል አቋቁሟል።

ግብረ ሀይሉ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት፤ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ፤ ከአካባቢጥበቃ ባለስልጣን፤ ከንግድ ቢሮ፤  ምግብ መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን የተውጣጣ ነው።

ግብረ-ሀይሉ መዲናውን በግድየለሽነት በሚያቆሽሹ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ከነገ ታህሳስ 1 ቀን ጀምሮ የተጠያቂነት እርምጃ መወሰድ እንደሚጀምር ግብረ ሀይሉ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ  ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ ፤ እንዳሉት  በመዲናው የከተማውን ጽዳት ለማስጠበቅ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የቁጥጥር ስራውን ነገ በይፋ ይጀምራል።

ግብረ ሀይሉ የህግ ተጠያቂነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዚህም ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ቆሻሻን የሚያስወግዱ ፤ አካባቢያቸውን የማይጠብቁ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ  አረጋግጠዋል።

የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ለማ በበኩላቸው፤ ቆሻሻን በህገ-ወጥ መንገድ በሚያስወግዱት ላይ የህግ ተጠያቂነት ለማስፈን የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አበባ እሸቴ፤ የህግ ተጠያቂነቱ ተግባራዊ መሆን መጀመሩ የከተማውን ፅዳት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ይረዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም