በሳዑዲ አረቢያ በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ 690 ኢትዮጵያውያን አገራቸው ገቡ

119
አዲስ አበባ ግንቦት12/2010 በሳዑዲ አረቢያ በጅዳና ጅዛን በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ 690 ኢትዮጵያውያን ትናንት ማምሻውን ወደ አገራቸው ተለመሱ። ኢትዮጵያዊያኑ በሶስት በረራዎች ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሳዑዲ ባደረጉት ጉብኝት በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ የሳዑዲ መንግሥት 1ሺህ ኢትዮጵያዊያን ለመልቀቅ በወሰነው መሰረት 900 ወንድና 100 ሴት እስረኞች ተለቀዋል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን በፍጥነት ተፈትተው ለአገራቸው መብቃታቸው ጉብኝቱ በዲፕሎማሲው መስክ የነበረውን  ስኬታማነት የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያዊያንኑን ለመቀበል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ጊዜያዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸው በዚህም ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲገቡ ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል። ''ከየትኛውም አገር ጋር የሚደረግ ግንኙነት በዜጎች ክብርና ሰብአዊ መብት ላይ የሚያተኩር ነው'' ያሉት ቃል አቀባዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ያደረጉት ጉብኝት በዚህ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አብራርተዋል። ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "መንግሥት ባደረገው ጥረት ለአገራችን እንድንበቃ በማድረጉ ጥልቅ ደስታ ተሰምቶናል" ሲሉ ተናግረዋል። 'እኛ ያገኘነውን ዕድል ያላገኙ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አሉ እነሱም እንዲመለሱ ጥረት ቢደረግ መልካም ነው' የሚል አስተያየትም አክለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም