የመራጮች ምዝገባን ከማንዋል ወደ ዲጂታል መቀየር የሚያስችል ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ ይፋ ሆነ

133

አዲስ አበባ(ኢዜአ)ህዳር 30/2015 የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባን ከማንዋል ወደ ዲጂታል መቀየር የሚያስችል ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ ይፋ አደረገ።

ቦርዱ ፕሮጀክቱን ለተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማስተዋወቅ ሊሻሻሉ በሚገባቸውና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ፕሮጀክቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የታዩ ችግሮችን ለማሻሻል ቦርዱ በትኩረት እየሰራ ነው።

በተጨማሪም የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ በማንዋል መሰራቱ ወጥ የሆነ የመረጃ አያያዝ እንዳይኖር ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የምርጫውን መጠናቀቅ ተከትሎ የተፈጠሩ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ቦርዱ ጥናት ማካሄዱን ገልጸው የመራጮች የምዝገባ ሂደት በመጀመሪያ ደረጃ ሊሻሻል እንደሚገባ በጥናቱ መለየቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህ ፕሮጀክት የመራጮች የምዝገባ ሂደትን በማዘመን፣  ሙሉ መረጃዎቻቸውን በማስፈርና የተሟላ ኦዲትን በመስራት ዘመናዊ አሰራርን ለማስረጽ ታልሞ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

የፕሮጀክቱን ምንነት፣ ዓላማውን ፣ አስፈላጊነቱንና አሁን ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት በቦርዱ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የስራ ኃላፊ አቶ ድሪባ መገርሳ ገለጻ አድርገዋል።

በዚህም የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ ሙሉ መረጃዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደገፈ አሰራር በማስቀመጥ የምርጫ ስርዓቱን ተዓማኒና ግልጽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በተለይም የመራጮችን የምዝገባና የመረጃ አያያዝ ወደ ዲጂታላይዜሽን መቀየር ዋነኛ ጉዳይ መሆኑ ታምኖበታል።

በመሆኑም የመራጮች ምዝገባና ሙሉ መረጃን በተሟላ መልኩ የሚይዝ አዲስ ቴክኖሎጂ መልማቱን ነው የገለጹት።

ይህ ቴክኖሎጂ በቀላሉ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲጠቀሙበት የሚያስችልና ከኢንተርኔት ውጪ  አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነውም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂውን በሙከራ ደረጃ ለመጀመር የሚያስችል የተሟላ አቅም እንዳለ ጠቁመው ለዚህም በመላ አገሪቱ 2 ሺህ 886  የምርጫ ጣቢያዎች መለየታቸውን አስታውቀዋል።

ለእነዚህ ጣቢያዎችም በቂ የሰው ኃይል፣ የግብአትና የመሰረተ ልማት አቅርቦት መሟላቱንም እንዲሁ።

የውይይቱ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው አገራዊ ሁኔታውንና የሌሎች አገራት ተሞክሮን በማካተት ለመተግበር የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በተጨማሪም ቴክኖሎጂው ለሳይበር ጥቃትና የደህንነት ችግር እንዳይጋለጥ ልዩ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

 ከቴክኖሎጂ አሰራር ጋር ቅርበት የሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችንም እንዲሁ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባም አመላክተዋል።

በተነሱት አስተያየቶች ላይ ምክትል ሰብሳቢው አቶ ውብሸት አየለ በሰጡት ምላሽ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በሙከራ ደረጃ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለይም ይህ ቴክኖሎጂ ከምርጫ ሂደት ጋር ፍጹም ተያያዥነት እንደሌለውና የመራጮች ምዝገባ ላይ ብቻ ትኩረት እንደሚያደርግም አስገንዝበዋል።

በዚህም የምርጫ መጭበርበርን እንዲሁም የተመራጭ ፓርቲዎችና ግለሰቦችን መረጃ የሚያካትት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ይህ ፕሮጀክት ከመራጮች መረጃ ጋር ተያይዞ የነበሩ ክፍተቶችን የሚሞላና የኦዲት ስራውን በተቀላጠፈ መልኩ የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም