ማሕበረሰቡ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ዜጎችን ከመደበቅ ይልቅ ወደ ሕክምና ማዕከላት ወስዶ ማሳከም አለበት - የዘርፉ ምሁራን

282

ሐረር (ኢዜአ)  ህዳር 30/2015 ማሕበረሰቡ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ዜጎችን ከመደበቅ ይልቅ ወደ ሕክምና ማዕከላት ወስዶ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ  አለበት ሲሉ የዘርፉ ምሁራን ገለፁ፡፡

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የአገር ውስጥ እና የውጭ የስነ-አእምሮ ህክምና ከፍተኛ ባለሞያዎች የተሳተፉበት በአዕምሮ ጤና ላይ ያተኮረ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የስነ-አእምሮ ህክምና መምህር እጩ ዶክተር ፈቲያ መሃመድ በአገራችን ለአዕምሮ ህክምና የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው ይላሉ፡፡

ማህበረሰቡ ጋር ባለው አነስ ያለ ግንዛቤ ምክንያት የአዕምሮ ህመም ተጠቂዎችን አስሮ በማስቀመጡ፤ ከቤት ማባረሩ ችግሩን እያባባሰው መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሄን አይነት ችግር የሚገጥማቸውን ዜጎች አስሮ ከማስቀመጥ ይልቅ ወደ ህክምና መውሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላው በአሜሪካ ሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ህክምና ዘርፍ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ናሆሚ አብዱረህማን በበኩላቸው በአገራችን ለአዕምሮ ጤና የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ ማህበረሰቡ ለአዕምሮ ሕመም ተጠቂዎች በቂ እንክብካቤ አያደርግም ብለዋል።

ለአዕምሮ ህመም ተጠቂዎች አስፈላጊውን እንክብካቤ መስጠት ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለውም ተናግረዋል።

የአዕምሮ ህመም በዓለም ላይ በርካቶች የሚጠቁበት ቢሆንም በኢትዮጵያ ለተጠቂዎች ተገቢው እንክብካቤ አለመደረጉ ችግሩን እያባበሰ ይገኛል ያሉት ደግሞ የሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባው ፕሮፌሰር አሪፍ አህመድ ናቸው።

''ችግሩን ለመከላከል ቀዳሚ መፍትሄው የማህበረሰቡ ድጋፍ ነው'' የሚሉት ፕሮፌሰሩ የአዕምሮ ህመም ተጠቂዎችን ከማግለል ይልቅ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

ማህበረሰቡ ብሎም ተመራማሪዎች ተቀራርበው እንዲሰሩ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ ቀጣይ ስራ መሆኑን ፕሮፌሰር አሪፍ ገልጸዋል፡፡

የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተሳትፎ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ይስሃቅ ዩሱፍ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከአዕምሮ ህመም ጋር በተያያዘ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የአዕምሮ ህክምና ማእከል በአዴሌ ላይ ማቋቋሙን ገልፀዋል።

ተቋሙ ሲቋቋም በአዴሌ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች ቢሆንም የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲገለገልበት ታሳቢ የተደረገ  ነው ብለዋል።

ለሶስት ቀናት በሚዘልቀው ጉባዔ በዘርፉ የተከናወኑ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም