የመጀመሪያው የኢሬቻ የሰላም ሽልማት ተካሔደ

80
አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 በመጀመሪያው የ'ኢሬቻ የሰላም ሽልማት' ስምንት ሰዎችና አንድ ቡድን በሰላም ዙሪያ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሽልማት ተበረከተላቸው። የኢትየጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የኢሬቻ በዓል ዋዜማን ምክንያት በማድረግ መርሃ ግብሩን አዘጋጅተዋል። በዚህ በመጀመሪያው የኢሬቻ የሰላም ሽልማት ላይ ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስና ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ፈቃደኛ ሆነው ለሁለት ተከፍሎ የነበረውን ሲኖዶስ አንድ በማድረግ ረገድ ላበረከቱት አስተዋዕኦ ተሸላሚ ሆነዋል። በተመሳሳይ የኡላማዎች ምክር ቤት ኃላፊ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ በህዝበ ሙስሊሙ መካከል ያለውን ልዩነት ለማስወገድ እየሰሩ ባሉት ስራ የሰላም ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋል። አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ የኦሮሞ ወጣቶችን በመምከርና በማስተባበር ወጣቱ ሰላሙን እንዲጠብቅ ባደረጉት ጥረት፣ ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሓመድ በሱማሌ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በሰሩት ስራ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙሪያ ቡራዩ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ሰፍቶ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዳያመራ ተከላክለው ሰላም እንዲሰፍን በማድረጋቸው በቡድን የሰላም ሽልማቱን ተቀብለዋል። በሌላ በኩል አርቲስት መሓሙድ አህመድ፣ አርቲስት አሊ ቢራ እንዲሁም ሰዓሊ ለማ ጉያ በስራቸው ውስጥ ለሰላም በሰጡት ትኩረት የዚህ ሽልማት ተካፋይ ሆነዋል። የሰላም ተሸላሚዎቹ በበኩላቸው ሽልማቱ መመሰጋገንን የሚያበረታታና የበለጠ የአገሪቷን አንድነት የሚያጠናክር በመሆኑ መልካም ጅምር መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም አሁን የተጀመረው ለውጥ ዘላቂ እንዲሆን ሁሉም ሊተባበርና ሊተጋገዝ ይገባል ያሉ ሲሆን ህዝቡ ከቂምና ከበቀል ራሱን ማራቅ አለበትም ብለዋል። በሽልማት ስን ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ፎዚያ አሚን ሽልማቱ "የኢሬቻ በዓል በጥቅሉ የሰላም መገለጫ" መሆኑን ለማስገንዘብ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ በመላ አገሪቱ ለሰላም የተዋደቁትን፣ የለፉትን እንዲሁም ወደ ፊትም ለሰላም የሚተጉትን ለማበረታታትና በሌሎችም ዘንድ ለማስፋት ይረዳል ነው ያሉት። የኢሬቻ የሰላም ሽልማት ህዝቦች ኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የአንድነት፣ የይቅርታና የፍቅር መገለጫ መሆኑን እንዲረዱትና ሌሎችም በዓሉን እንዲጠብቁት ያስችላል ነው ያሉት። አያይዘውም ሚኒስትሯ የገዳ ስርዓት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ እንዲመዘገብ በጋራ ይሰራል ብለዋል። ከሁለት ዓመታት በፊት በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ህይወታቸውን ያጡ የበዓሉ ታዳሚዎች "ክብር ይገባቸዋል፣ ሊዘከሩም ይገባል" ብለዋል ሚኒስትሯ። በስነ ስርዓቱ ላይ ''ኢሬቻ የብዝሃነትና የአንድነት መሰረት'' በሚል ሃሳብ በኢሬቻ በዓል ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል። ጽሁፍ አቅራቢው አቶ ስንታዬሁ ቶላ የኢሬቻ እሴቶችን መነሻ በማድረግ "የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በልዩነት ውስጥ አንድነታቸው እንዲጎለብት ማድረግ ይቻላል" ብለዋል። ለዚህም በቀጣይ በኢሬቻ እሴቶች ዙሪያ ተጨማሪ ጥናቶችን ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም