ብልጽግና ፓርቲ ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል

222

አዲስ አበባ(ኢዜአ)ህዳር 30/2015 "ብልጽግና ፓርቲ ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ የፓርቲው ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ 1ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት በሐዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነገ ድረስ በሚቆየው ጉባኤ ላይ 1 ሺህ 116 የሚሆኑ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የፓርቲው ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፤ ፓርቲው በአንደኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ያስቀመጣቸውን ውሳኔዎች በመፈጸም ረገድ በርካታ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ከጉባኤው ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሶስተኛ ዙር ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው፤ ፓርቲው እነዚህን ፈተናዎች በድል በመሻገር አገርን ከፍ ያደረጉ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል፡፡

ለአብነትም በጉባኤው "ኢትዮጵያ ስንዴ ኤክስፓርት ማድረግ አለባት" የሚል ውሳኔ መቀመጡን ጠቅሰው፤ በዘንድሮው ዓመት ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን ለወጪ ንግድ ማቅረብ እንደምትጀምር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በፓርቲው 1ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ገቢራዊ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል ትምህርት የሰጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በርካታ አባላትን በመያዝ ግን በአህጉር ዓቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በአፍሪካ በህዝብ ቁጥር ቀዳሚ ከሚባሉ አገራት ተርታ የምትሰለፍ አገር እየመራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በቀጣይ በርካታ ስራዎች ይጠበቁበታል ነው ያሉት፡፡

ለዚህ ደግሞ እውቀትና ክህሎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እርስ በርስ በመደማመጥ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የማደግ ተስፋ ያላት ታላቅ አገር መሆኗን የገለጹት የፓርቲው ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ ለኢትዮጵያ የእድገት ጉዞ እንቅፋት የሆኑ ትርክቶችን መቅረፍ እንደሚገባ አብራርተዋል፡

በተለይ ያለፉ ታሪኮች የግጭትና የመለያየት ምንጭ መሆን እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከትናንት ታሪኮች ትምህርት በመውሰድ እንዳይደገሙ መስራትና የተሻለ ነገን ለመገንባት በጋራ መቆም ይገባል ነው ያሉት፡፡

ያጋጠመንን ጦርነት በተቀናጀ መንገድ በጋራ መመከት እንደቻልን ሁሉ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥም የበኩላችንን ሚና ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ሌብነት ላይ የተጀመረው ትግልም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡


በቀጣይ የፓርቲው አባላት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች እንዲሳኩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ፓርቲው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በበኩላቸው ፓርቲው ያካሄደውን አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተከትሎ ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ከጊዜያዊ መፍትሄ ባሻገር እንደ ስንዴ ልማት ባሉ ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ከፍተኛ ስራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡

የፓርቲውን ውስጠ-ዴሞክራሲ የሚያጠናክሩ ስራዎችን በማከናወን ረገድም የተሻለ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ለዴሞክራሲ ተቋማት መጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ፓርቲው በአስቸኳይ ጉባኤው የምርጫ ቦርድ የሰጠውን የማስተካከያ ሃሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም