በክልሉ የማዕድን ሃብቱን ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማዋል ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው

104

ባህር ዳር (ኢዜአ)  ህዳር 30 ቀን 2015 በአማራ ክልል ያለውን የማዕድን ሃብት ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማዋል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የተጀመረው የተቀናጀ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የስነ ምህዳር ካርታ ስራና የማዕድን ፍለጋ ክምችት ግመታ ጥናት ለማካሄድ የስነ ምድር ጥናት ትምህርት ክፍል ከፍተው ከሚያስተምሩ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ በስምምነት ስነ ስርዓቱ እንዳሉት፤ መንግስት በቀየሰው የአገር በቀል ኢኮኖሚ መርሃ ግብር የማዕድን ዘርፉ ከግብርናና ኢንዱስትሪ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ ተቀምጧል።

ይህም በክልሉ ያለውን የማዕድን ሃብት ያለበትን ቦታ በጥናት በመለየት፣ ክምችቱን በማወቅና ለአልሚ ባለሃብቶች በማስተላለፍ ለአገር እድገትና ብልጽግና ለማዋል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የማዕድን ዘርፉ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስና ለዜጎች አዳዲስ የስራ እድል በመፍጠር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ እስካሁን የማዕድን ክምችቱን በጥናት ለይቶ በማልማት ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ አንደሚገኝ አስገንዝበው የዩኒቨርሲቲዎችን አቅም በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት የጋራ ስምምነት ማካሄድ አስፈልጓል ብለዋል።

ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተደረሰው የስነ ምህዳር ካርታ ስራና የማዕድን ፍለጋ ክምችት ግመታ ጥናት በተያዘው ዓመት መጨረሻ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለውጤታማነቱ በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በቢሮው የማዕድን ክምችት ግመታ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አስፋው በስምምነቱ ወቅት ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳሉት ከባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ደብረ ብርሃንና ወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተደረሰው ስምምነት ከ6 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት በላይ የስነ ምድር ካርታ ስራና በ336 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ የማዕድን ፍለጋ ጥናት ለማካሄድ ያስችላል።

በስምምነቱ መሰረትም ከሚጠኑት 12 ፕሮጀክቶች ውስጥ ለሰባቱ ቢሮው 20 ሚሊየን ብር የበጀተ ሲሆን ቀሪዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው ወጭ የሚያካሂዷቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጥናቱም በዋግ ኽምራ፣ አንኮበር፣ ጃናሞራ፣ ጓንጓና ሌሎች የማዕድን ክምችት አለባቸው ተብሎ በሚገመቱ አካባቢዎች እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተስፋዬ ሽፈራው በበኩላቸው ስምምነቱ የመንግስት ቢሮዎችንና ዩኒቨርሲቲዎችን በማስተሳሰር በአገራዊ እድገቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ነው።

ዩኒቨርሲቲው ያለውን አቅም በመጠቀም የተሰጡትን ፕሮጀክቶች በተያዘው ጊዜ አከናውኖ ለማስረከብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የማዕድን ጥናቱ በመስክ ስራና በላብራቶሪ ተደግፎ የሚከናወን በመሆኑ የዘርፉን ምሁራን አቅም የሚገነባና የተሻለ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል ልምድ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የተካሄደው ስምምነት በክልሉ ያለውን የስነ ምድር ካርታ ስራ ከ30 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይና የማዕድን ፍለጋውን ደግሞ 1 ሺህ 120 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ እንደሚያደርሰው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም