የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና በመጪው ሰኔ በተመሳሳይ ጊዜ ይሰጣል ትምህርት ሚኒስቴር

341

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ ተመራቂ ተማሪዎች በመጪው ሰኔ ወር በተመሳሳይ ግዜ እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ፈተናው በሁሉም የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለሚገኙ 200 ሺህ ተመራቂ ተማሪዎች በኦንላይን እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

በሚኒስቴሩ የትምህርት አካዳሚ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጋጀ አውደጥናት ላይ እንደገለጹት መውጫ ፈተና በመጪው ሰኔ ወር ለሁሉም ቅድመ መደበኛ ተመራቂ ተማሪዎች በአንድ ጊዜ ይሰጣል።

የመጀመሪያው ፈተና በሰኔ ወር ከተሰጠ በኋላ ቀጣዩ የመውጫ ፈተና ከስድስት ወራት በኋላ እንደሚሰጥም ዶክተር ኤባ አስረድተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ዴስክ ኃላፊ አቶ ሰይድ መሀመድ በበኩላቸው ፈተናው ለሁሉም ተማሪዎች በኦንላይን እንደሚሰጥ ጠቅሰው ይህም የፈተና ስርቆትን ለመከላከል የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱም ሆኑ ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናው በተመሳሳይ ጊዜ በኦንላይን እንደሚሰጥ አውቀው ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉም አቶ ሰይድ አሳስበዋል።

በመውጫ ፈተና ብቃትና የፈተና ኮርሶች ልየታና የተገቢነት ማረጋገጥ ዙሪያ በተዘጋጀው አውደ-ጥናት ከሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መምህራን መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም