ኢጋድ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ ተጨባጭ ተግባር አከናውኗል

109

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 ኢጋድ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ።

ኢጋድ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር የ2022 ዓመት አፈፃፀምና ቁልፍ ስኬቶች ላይ እንዲሁም 2023 በጀት ላይ ውይይት አድርጓል።

የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢጋድ አምባሳደሮችና ባለሙያዎች ስብሰባ በቁልፍ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

ኢጋድ ሊጠናቀቅ በተቃረበው የፈረንጆች ዓመት በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ባደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቧል ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት መሪነት የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር የደረሰው የሰላም ስምምነት እንዲሁም በሱዳን ሰላም ለማስፈን የተደረገው ስምምነት ለቀጣናው በስኬት የሚመዘገቡ ናቸው ብለዋል።

የቀጣናው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው የማድረግ ሃላፊነት በኢጋድ ላይ አርፏል ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፤ ይሄንን ለማንቀሳቀስ የፋይናንስ አቅም ማጎልበት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በ2022 ዓመት የኢጋድ በጀት 10 በመቶ እድገት እንደነበረው ገልጸው የቀጣዩ 15 በመቶ ማደጉ የአባል አገራትን ቁርጠኝነት የሚያሳይና የኢጋድን ተሳትፎ የሚያጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የአባል አገራት ለኢጋድ የሚደርሰውን በጀት በወቅቱና አሟልቶ በማቅረብ ሂደት ያለባቸውን ውስንነት ማሻሻል አለባቸው ብለዋል።

የአባል አገራት የፋይናንስ አቅርቦት ቀጣናዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ዋና ጸሃፊው ጠቅሰዋል።

የአባል አገራቱ ካፀደቁት በጀት መካከል ማቅረብ የቻሉት 42 በመቶውን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢጋድ የሚያደርገው ተቋማዊ ለውጥ 90 በመቶ ደርሷል፣ ቀሪው ደግሞ የአባል ሀገራትን ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ኢጋድ ከ2021 እስከ 2025 ያለውን ስትራቴጂክ ዕቅድ በስኬት ለማጠናቀቅ የፋይናንስ አቅሙ መጠናከር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም