ለወባ ተጋላጭ አካባቢዎች 295 ሺህ የአልጋ አጎበር በስርጭት ላይ ነው -መምሪያው

205

መተማ (ኢዜአ)  ህዳር 30/2015 ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች 295 ሺህ የአልጋ አጎበር በስርጭት ላይ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የወባ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ ወርቁ መንግስቴ ለኢዜአ እንዳሉት የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል እየተሰራ ነው።

በዞኑ ከህዳር 26 ቀን 2015 ዓም ጀምሮ ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አራት ወረዳዎችና ሶስት ከተማ አስተዳደሮች 295 ሺህ የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል ።

እየተሰራጨ ባለው የአልጋ አጎበር ከ400 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ከበሽታው እንደሚጠበቁ አመላክተዋል።

በተለይም የክረምቱን መውጣት ተከትሎ የበሽታው ስርጭት በበረታባቸው ምዕራብ አርማጭሆ፣ ቋራና መተማ ወረዳዎች ከአጎበር ስርጭቱ ጎን ለጎን በቤት ለቤት ጉብኝት በሚደረግ የሙቀት ልኬት መሰረት  የወባ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳዎቹ 90 ሺህ 545 መኖሪያ ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ጠቅሰዋል።

ባለፈው አመት ከ90 ሺህ በላይ አጎበር መሰራጨቱን አስታውሰው "አካባቢው ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለበት በመሆኑ ጠንካራ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ይገኛል" ሲሉ ባለሙያው አሰታውቀዋል።

የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ስለእናት አስማረ ያገኙትን አጎበር በአግባቡ እንደሚገለገሉበት ተናግረዋል ።

ለአምስት የቤተሰብ አባላት ሦስት አጎበር በነፃ እንደተሰጣቸው የገለጹት ደግሞ የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ አቶ ተረፈ ሙሉቀን ከዚህ በፊት አጎበርን ለሌላ ተግባር ይጠቀሙበት እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን በትክክል በመጠቀም የወባ ትንኝን እንደሚከላከሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም