የሰላም ስምምነቱ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ፈጥሯል

239

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ህዳር 30/2015 የሰላም ስምምነቱ ለሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው መነቃቃት መፍጠሩን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ገለጹ።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት መፍጠሩን የዘርፉ ተዋናዮች ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዘው የነበሩ ክልከላዎች መቀነሳቸው ዘርፉን ወደ ነበረበት እንቅስቃሴ ለመመለስ የራሱን በጎ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በዘርፉ የሚታይ ለውጥ እየመጣ መሆኑን የካሌብ ሆቴልና የታላቋ ኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ኃላፊዎች ገልጸዋል።

አሁን ላይ በአገሪቱ የሚታየው ሁለንተናዊ የለውጥ ሂደት ለኢንዱስትሪው የተሻለ እንቅስቃሴ እያመጣ መሆኑን የካሌብ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ጌታብቻ ደጀኔ አስታውቀዋል።

ለጉብኝትና ለሥራ ጉዳይ ወደ አገሪቱ እየገቡ የሚገኙ የውጭ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያዉያን ዳያስፖራዎች ለዘርፉ መነቃቃት መፍጠራቸውን ተከትሎ የሆቴል ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመሩን ጠቅሰዋል።

በተለይም ከጎረቤት አገሮች የሚመጡ ተጓዦችና ጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩን አቶ ጌታብቻ አመልክተዋል።

ግጭቱን ተከትሎ የውጭ መንግስታት ባልተጨበጠ ሁኔታ ለዜጎቻቸው የሚሰጧቸው መግለጫዎች በዘርፉ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

የታላቋ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል ተስፋዬ በበኩላቸው በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት የመስተንግዶው ኢንዱስትሪ ላይ ጫና ማሳረፉን አስታውሰዋል።

የሰላም ሥምምነቱ ከተፈረመ ጀምሮ ጎብኚዎች በኢሜልና በስልክ የጉብኝት ጥያቄዎች እያቀረቡ እንደሚገኙ አቶ ዳንኤል አስታውቀዋል።

በኢንዱስትሪው ላይ ተስፋ ሰጪና ለብዙዎችም የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል አቅም መፈጠሩንም ጨምረው ገልጸዋል።

አቶ ዳንኤል አያይዘውም አሁን እየተፈጠረ ያለው መረጋጋት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ትልቅ ሀብት መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባና በዙሪያዋ አዳዲስ የመስህብ ሥፍራዎች መገንባታቸውና ነባሮችን የማበልጸግ ሥራዎች መከናወናቸው ለወደፊቱ በኢትዮጵያ የመስተንግዶ ኢንዱስትሪ የራሳችንን አስተዋጽኦ እንድናደርግ ያነሳሳናል ብለዋል።

ከኮቪድና ከሰሜኑ ግጭት ተጽዕኖ በመውጣት በዘርፉ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አብዛኞቹ የአስጎብኚ ድርጅቶች በኮቪድና በጦርነቱ ምክንያት ችግር ላይ በመውደቃቸው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም