በአዳማ ከተማ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

220

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 ባለፉት አራት ወራት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የአዳማ ከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ገለፀ።

የከተማዋ ገቢዎች ባለስልጣን ሀላፊ አቶ በላቸው አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው በጀት ዓመት የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ለመሸፈን 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

በዚህም ባለፉት አራት ወራት ከመደበኛ ገቢና መዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 2 ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስነጻጸር የ1 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸው ለዚህ ደግሞ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ወቅቱን ጠብቆ ግዴታውን በመወጣቱ ነው ብለዋል።

አምና ዓመቱን ሙሉ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተሰበሰበ አቶ በላቸው ገልጸዋል።

የግብር አሰባሰብ ሂደትን የሚያሳልጡ አሰራሮችን በመተግበር ረገድ በአስተዳደሩና በስሩ ባሉት ስድስት ክፍለ ከተሞች በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የግብር ከፋዩን ፋይሎች 'ከሃርድ ኮፒ' ወደ 'ሶፍት ኮፒ' በመቀየር የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ደንበኞች ካሉበት ሆነው በቴሌ ብር እንዲከፍሉ ለማስቻልና የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን ከሌብነት ነፃ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከግብር ከፋዮች አንጻርም የቫት ተመዝጋቢዎች የሽያጭ ደረሰኝ ያለመስጠት፣ ከሽያጭ በታች ደረሰኝ መቁረጥና ግብርን በወቅቱ ያለማሳወቅ አሁንም የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የከተማዋ ግብር ከፋዮች በበኩላቸው የባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከግብር ከፋዮቹ መካከል አቶ ቢንያም ዳንኤል በሰጡት አስትያየት አስተዳደሩ አሁን እየሰጠ ያለው አገልግሎት ከነበረው የተሻለና ፈጣን በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

''ግብር መክፈል የሀገሪቷን ልማትና እድገት ያፋጥናል'' ያሉት አቶ ቢንያም ''ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ህጋዊ ደረሰኝ ከማዘጋጀትና ከመስጠት ጀምሮ ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት'' ብለዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ግብር ከፋይ አቶ ዮሐንስ ጋረደው፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል።

This image has an empty alt attribute; its file name is ተገል.jpg

ሀገር የሚለማውና እድገትም የሚኖረው በታማኝነትና በቅንነት ግብር መክፈል ሲቻል በመሆኑ ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።

ሆኖም አሁንም አንዳንድ ክፍለ ከተሞች ላይ የአገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችና የተጋልጋዩ ቁጥር ስለማይመጣጠን መስተካከል እንዳለበት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም