በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለታቀፈችው የጎርጎራ ከተማ የተዘጋጀ መዋቅራዊ ፕላን የሙከራ ትግበራ ተጀመረ

175

ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 30 ቀን 2015 በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለታቀፈችው የጎርጎራ ከተማ የተዘጋጀ የ10 ዓመት መዋቅራዊ ፕላን የሙከራ ትግበራ መጀመሩን የከተማዋ መሪ ማዘጋጃ ቤት ገለጸ፡፡

መዋቅራዊ ፕላኑ የከተማዋን ቀጣይ የቱሪዝም ፣ የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚና እድገት ታሳቢ ያደረገ  መሆኑን የማዘጋጃ ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ተገኘ ሙሉ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የከተማዋን የቆዳ ስፋት ቀድሞ ከነበረበት 400 ሄክታር ወደ 7ሺ 246 ሄክታር እንዳሳደገ ጠቅሰው፤ የመዋቅራዊ ፕላኑ የሙከራ ትግበራ የተጀመረው በተያዘው  ወር መሆኑን አስታውቀዋል።

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ይዞት በመጣው የልማት ትሩፋት አሁን ላይ በከተማዋ በርካታ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚያቀርቡትን የቦታ ጥያቄ ለማስተናገድም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በከተማው የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የቆየውን የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቦታና የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡   

''መዋቅራዊ ፕላኑ የከተማውን የወደፊት ፈጣን የልማት እድገት ታሳቢ በማድረግ ሳይንሳዊ አሰራሩን መሰረት በማድረግ የተዘጋጀ ነው'' ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን መስፍን ናቸው፡፡

መዋቅራዊ ፕላኑ በጎርጎራ አካባቢ የሚገኙ ገዳማትን ፣ታሪካዊ ቦታዎችና የቱሪዝም ሀብቶችን እንዲሁም የጣና ሀይቅን ብዝሃ ህይወት ግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የከተማውን ኢንቨስትመንት ለማፋጠን እንዲሁም የቱሪዝም ሀብቶችን ለማልማት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ 30 የዘርፉ ምሁራንን በማሳተፍ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

መዋቅራዊ ፕላኑ የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ፣የመኖሪያና የንግድ አካባቢዎችን፣ የመዝናኛና የኢንዱስትሪ ዞኖችን እንዲሁም የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለማስፋፋትም ሆነ ለመገንባት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

የጎርጎራ ከተማ ህዝብና የምክር ቤት አባላት በመዋቅራዊ ፕላኑ ረቂቅ ዝግጅትና ንድፍ ላይ ግብዓት እንዲሰጡ ከተደረገ በኋላ በክልሉ ፕላን ኢንስቲትዩት መጽደቁን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በመዋቅራዊ ፕላኑ የሙከራ ትግበራ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ፈጥኖ መፍታት እንዲቻልም በአሁኑ ወቅት በማማከር ስራ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከተቆረቆረች ከ700 ዓመት በላይ የሆናተ የጎርጎራ ከተማ በአሁኑ ወቅት 30ሺህ የሚጠሃ ህዝብ እንደሚኖርባት ከመሪ ማዘጋጃ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም