የእግር ኳስ ኃያላኑን ያገናኘው የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች

279

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 30 ቀን 2015 በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከሁለት ቀን እረፍት በኋላ ዛሬ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ይመለሳል።

ብራዚል ከክሮሺያ ኔዘርላንድስ ከአርጀንቲና የሚያደርጓቸው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች በጣም ተጠባቂ ናቸው።

ከምሽቱ 12 ሰአት በኢጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም ብራዚል ከክሮሺያ የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ቀልብ የሳበ ጨዋታ ነው።

ብራዚል በጥሎ ማለፉ ኮሪያ ሪፐብሊክን እንዲሁም ክሮሺያ ጃፓንን በማሸነፍ ነው ለሩብ ፍጻሜ ያለፉት። ሁለቱ አገራት በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

እ.አ.አ 2006 ጀርመን ባሰናዳችው 18ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ስድስት ተገናኝተው ብራዚል ኮከብ ተጫዋቿ ካካ በ44ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ክሮሺያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ብራዚል እ.አ.አ በ2014 ባዘጋጀችው 20ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው በኔይማር ሁለት ግቦች እንዲሁም ኦስካር ባስቆጠራት አንድ ግብ ክሮሺያን 3 ለ 1 ማሸነፏ ይታወሳል።

ለክሮሺያ የብራዚሉ ማርሴሎ ቪዬራ ነበር በራሱ ግብ ላይ ያስቆጠረው።

የዓለም ዋንጫውን ጨምሮ ብራዚልና ክሮሺያ እስከ አሁን አራት ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተው ብራዚል ሶስት በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች።

ቀሪው አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በአራቱ ጨዋታዎች ብራዚል ሰባት እንዲሁም ክሮሺያ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

የ37 ዓመቱ እንግሊዛዊ ማይክል ኦሊቨር የሁለቱን አገራት ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

ከምሽቱ 4 ሰአት 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሉሳይል ስታዲየም አርጀንቲና ከኔዘርላንድስ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

አርጀንቲና አውስትራሊያን እንዲሁም ኔዘርላንድስ አሜሪካን በጥሎ ማለፉ በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜው ደርሰዋል።

ሁለቱ አገራት በዓለም ዋንጫው ከዚህ ቀደም ለአምስት ጊዜ ተገናኝተዋል።

እ.አ.አ 1974 ጀርመን (በወቅቱ ምዕራብ ጀርመን) ባዘጋጀችው 10ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ተገናኝተው ኔዘርላንድስ በቀድሞ ኮከቧ ዮሐን ክሩፍ ሁለት ግቦች እንዲሁም ሩድ ክሮልና ጆኒ ሬፕ ባስቆጠሯቸው አንድ አንድ ጎሎች አርጀንቲናን 4 ለ 0 መርታት ችለዋል።

ኔዘርላንድስ በወቅቱ ዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሳ በጀርመን (በወቅቱ ምዕራብ ጀርመን) 2 ለ 1 ተሸንፋለች።

ከአራት ዓመት በኋላ አርጀንቲና ባዘጋጀችው 11ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከኔዘርላንድስ ጋር በፍጻሜው ተገናኝታ በማሪዮ ኬምፐስ ሁለት ግቦች እና ዳንኤል ቤርቶኒ ባስቆጠራት አንድ ግብ 3 ለ 1 በማሸነፍ ዓለም ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ አነሳች።

እ.አ.አ 1998 ፈረንሳይ ባዘጋጀችው 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜ ተገናኝተው ፓትሪክ ክላይቨርትና ዴኒስ ቤርካምፕ ባስቆጠሯቸው ግቦች ኔዘርላንድስ አርጀንቲናን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።

ክላውዲዮ ሎፔዝ ለአርጀንቲና ግቧን ያስቆጠረ ተጫዋች ነበር።

አርጀንቲና እና ኔዘርላንድስ እ.አ.አ 2006 ጀርመን ባዘጋጀችው ዓለም ዋንጫ በምድብ ሶስት ተገናኝተው ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ሁለቱ አገራት ለመጨረሻ ጊዜ በዓለም ዋንጫው የተገናኙት ብራዚል እ.አ.አ በ2014 ባስተናገደችው 20ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ነበር።

በግማሽ ፍጻሜ በተደረገው ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜና በጭማሬ 30 ደቂቃ ግብ ባለመቆጠሩ ወደ መለያ ምት አምርቶ አርጀንቲና 4 ለ 2 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች።

ሁለቱ አገራት ዓለም ዋንጫውን ጨምሮ እስከ አሁን ዘጠኝ ጊዜ እርስ በእርስ የተገናኙ ሲሆን ኔዘርላንድስ አራት ጊዜ በማሸነፍ ከፊል የሆነ ብልጫ ወስዳለች።

አርጀንቲና ሶስት ጊዜ አሸንፋለች። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።በዘጠኙ ጨዋታዎች ኔዘርላንድስ 13 እንዲሁም አርጀንቲና ስድስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

የ45 ዓመቱ ስፔናዊ አንቶኒዮ ማቲዩ ላሆዝ የሁለቱን አገራት ተጠባቂ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች ማክሰኞ ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም