የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላምታን ላማምራ ጋር ተወያዩ

264

አዲስ አበባ ህዳር 30/2015 (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላምታን ላማምራ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ተወያዩ።

አምባሳደር ብርቱካን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩት በአልጄሪያ ኦራን ከተማ እየተካሄደ ካለው 9ኛው የአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት ጉባኤ ጎን ለጎን በተገናኙበት ወቅት ነው።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያ በመጪው መጋቢት ወር 5ኛውን የኢትዮ-አልጄሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ ማዘጋጀት የሚያስችላትን ዝግጅት መጀመሯን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል።

የአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላምታን ላማምራ በበኩላቸው የአልጄሪያንና የኢትዮጵያን መልካም ወዳጅነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማሳደግ በቅርቡ የሚካሄደው የሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አፍሪካ በሰላምና ደህንነት ላይ የሚገጥሟትን ችግሮች ለመፍታት በምታደርገው ጥረት የአልጄሪያ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ስለድጋፉ ማመስገናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም