በኢትዮጵያ የሚደረጉ የህግ ማሻሻያዎች ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጠየቀ

56
አዲስ አበባ   መስከረም 18/2011 በኢትዮጵያ የሚደረጉ የህግ ማሻሻያዎች ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ ምሁራን የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጠየቀ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ "ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት የፍርድ ቤቶች ሚና" በሚል ርዕስ ስምፖዚየም አካሂዷል። በዚሁ ጊዜ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዬ ደንደአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት እየተደረጉ ያሉት የህግ ማሻሻያዎች ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ ምሁራን ጥልቅ ጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ''ይህም በአገሪቱ ያሉ ተቋማትና ሴክተሮች ጤናማ  ሆነው እንዲሁም ተጣጥመው እንዲጓዙ ያደርጋል'' ብለዋል። መንግስት በአሁኑ ወቅት  በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የፍትህ ምክር ቤት አቋቁሞ የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ስራዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ምሁራን እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። ምሁራኑ በጥናትና ምርምር የተደገፈ አስተዋጽኦ ማድረግ ከቻሉ የህግ ማሻሻያዎቹ ዘመን ተሻጋሪ እንደሚሆኑም ተናግረዋል። የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳሳ ቡልቻ እንደተናገሩት፤ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የፍትህ ጥያቄዎችን ለመመለስ አገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በፍትህ ለመመልስ የህግ ስርዓቱን ማሻሻል የግድ ይላል። ስለሆነም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ግልጽ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር፣ ህዝቡ ህጎችን እንዲያውቅ ማድረግ፣ ህጎቹ ሁሉንም ዜጋ ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲያገለግሉ ማድረግ ዴሞክራሲያዊሽግግሩን የተሟላ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል። ''እየተካሄዱ ያሉ የህግ ማሻሻያዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉን ዓቀፍና ከፍርድ ቤቶች የመነጩ መሆን ይገባቸዋል'' ብለዋል። በሲምፖዚየሙ ላይ ከዋሽንግተን ሊ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ወረቀት አቅራቢ ዶክተር ሄኖክ ጋቢሳ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በፍርድ ቤት አስተዳደር፣ በህግ አውጭ፣ በህግ አስፈጻሚና በህግ ትምህርት ስርዓት ላይ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች ሲሰሩ  እንደነበር ጠቁመው የተሰሩት የለውጥ ስራዎች የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ስለነበረባቸው ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም ሲሉ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የሚደረጉ የህግ ማሻሻያዎች ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ  አገር አቀፍ ጥናቶች፣ ፍርድ ቤቶች ህገ መንግስቱን በተሟላ መልኩ እንዲያከናውኑ ስልጣን የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። ማሻሻያው ህዝቡ የሚያቀርበውን የፍትህ ጥያቄ ፍርድ ቤት እንዲመልስለት የሚያስችልና በተቋሙ ላይ እምነት የሚያሳድር መሆን እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል። ሲምፖዚየሙ በነገው እለትም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም