ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

97

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ልዩ ልዩ የትብብር መስኮች በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ተገለጸ።

በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት የተካሄደው 8ኛው የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

የሁለቱ ሀገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የልማት እቅዶችን ወደ ትግበራ በማስገባት የሁለትዮሽ የትብብር መስክን ማስፋት ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ሩሲያ በትምህርት፣ በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን ዘርፍና በሌሎችም የልማት ሥራዎች ዙሪያ ኢትዮጵያን እያገዘች መሆኑ ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፤ ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢኮኖሚ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች የልማት ትብብሮች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በሩሲያ ፒተርስበርግ ከተማ በተካሄደው በ7ኛው የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ከተደረሱ ስምምነቶች መካከል እስካሁን ያልተከናወኑት እንዲፈጸሙ ለማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።

ሁለቱ ሀገራት በሳይበር ደኅንነትና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉበት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውም ተመላክቷል።

የሩሲያ የፌዴሬሽን ልዑክ መሪ ኤቭጌኒ ፔትሮቭን፤ ሩሲያ በአፍሪካ አህጉር የልማትና እድገት እቅድ ላይ እገዛ በማድረግ የበኩሏን ሚና እየተወጣች ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በጤና እና ሌሎችም ዘርፎች ትብብራችንን እናጠናክራለን ብለዋል።

በማዕድን፣ በኃይል ልማት፣ በንግድ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በጂኦ-ስፓሻል እና በስፔስ ሳይንስም እንዲሁ።

በጤናው ዘርፍም አንዲሁ ሩሲያ ለኢትዮጵያ የባልቻ ሆስፒታልን ለመደገፍ የሚያስችል ስምምነት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እና የሩሲያ ቀይ መስቀል ፕሬዝዳንት ፓቬል ሳቭቹክ ፈርመዋል።

ስምምነቱ ሩሲያ ለባልቻ ሆስፒታል ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ድጋፍ የማድረግና ከሩሲያ የሕክምና ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ልምድ ማጋራት የሚያስችል መሆኑን ዶክተር ደረጄ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ124 ዓመታት በላይ በጠንካራ ወዳጅነት የዘለቀ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም