ፈረንሳይ በ1960ዎቹ ከኢትዮጵያ በውሰት የወሰደቻቸውን ቅርሶች መለሰች

183

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 ፈረንሳይ በ1960ዎቹ  ከኢትዮጵያ በውሰት የወሰደቻቸውን ቅርሶች በመመለስ ዛሬ ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ባለስልጣን አስረክባለች።

ቅርሶቹን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ የትብብር ኃላፊዋ ሶፊ ማካሜ ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አስረክበዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ተመላሽ የሆኑት ቅርሶች የእንስሳትና የድንጋይ መሳሪያዎች እንዲሁም የእንስሳት ቅሪተ አካል ናቸው።

ቅርሶቹ በፈረንሳዩ ተመራማሪ ዦን ሻቫዩ አማካይነት በመልካ ቁንጥሬና በኦሞ አካባቢ የተገኙ ሲሆን በ1960ዎቹ ወደ ፈረንሳይ ለተጨማሪ ጥናት በውሰት የሄዱ መሆናቸውንም አክለዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ የትብብር ኃላፊዋ ሶፊ ማካሜ በበኩላቸው፤ አጠቃላይ የተመለሱ ቅርሶች ብዛት 740 ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 28ቱ የእንስሳት ቅሪተ አካል ናቸው ብለዋል።

ቅርሶቹ ከ10 ሺህ እስከ ሁለት ሚሊዮን ዓመት ድረስ ያስቆጠሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ኃላፊዋ አክለውም ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በቅርስ ጉዳዮች መልካም ትብብር እንዳላቸው አንስተው፤ ይህንኑም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የቅርሶች አውደ ርዕይም የተካሄደ ሲሆን የአውደ ርዕዩ ዋና ዓላማም  ቅርሶቹን ያገኛቸው የፈረንሳይ ተመራማሪ ዦን ሻቫዩ  በህይወት ባይኖርም እሱን ለማሰብ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም