ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከቀጣናው ሀገራት ጋር ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች - ፕሬዝደንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ

212

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ፕሬዝደንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

24ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ስብሰባ ዛሬ በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሄድ ውሏል፡፡

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የሕብረቱ ስብሰባ ለቀጣናው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው በሽብር ወንጀል፣ በህገ-ወጥ የስዎችና የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በአደንዛዥ ዕጽ እና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዙሪያ በመምከር ላይ ይገኛል፡፡

የሕብረቱ ፕሬዝደንት በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሄራዊ ፖሊስ ዋና ኢንስፔክተር ጀነራል ዲዩዶኔ አሙሊ ባሂግዋ ኃላፊነታቸውን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስረክበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በሕብረቱ ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዝደንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃሎችን በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር በተለያዩ ጊዜያት በመሳተፍ ለዓለም አቀፍ ደህንነት ጭምር የራሷን አስታዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ከቀጣናው አገራት ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ፕሬዝደንቷ አክለውም በአሁኑ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ ድንበር ዘለል ወንጀሎች ደግሞ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሽብርተኝነት፣ ሙስና፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች ፈተና መሆናቸውን ገልጸው ይህን በጋራ መከላከል እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንት ሳህለ-ወርቅ በቀጣናው የሚገኙ የህግ አስከባሪ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

የሕብረቱ ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም የተደራጀ ወንጀልን መከላከል፣ የአባል ሀገራቱን የፖሊስ ህብረት ማጠናከር እና ሽብርተኝነትን መከላከል ላይ ከአቻ የፖሊስ አዛዦች ጋር በትብብር መስራታቸውን እንደሚያጠናከሩ አረጋግጠዋል።

በአፍሪካ ህብረት የኢንተርፖል ተወካይ ፍራንሲስ ዣቪየር ኢንተርፖል በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን እና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦችን ህብረት ለማጠናከር በርካታ ድጋፎችን ማድረጉን በመጥቀስ፡፡

ተቀማጭነቱን በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ ያደረገው ሕብረቱ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሕግ አስከባሪ ተቋማትን ትብብር የማጠናከር ዓላማን ይዞ እ.ኤ.አ በ1998 በኡጋንዳ ካምፓላ መቋቋሙ ይታወሳል።

ሕብረቱ በአባል ሀገራት መካከል የመረጃ ልውውጥን ለማጎልበት፣ የጋራ ስትራቲጂ ለመንደፍ እና በቀጣናው ሰላም ለማስፈን በተለይም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመመከት ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሲሺየልስ፣ ሩዋንዳ፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኮሞሮስና ቡሩንዲ የሕብረቱ አባል ሀገራት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም