የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችና ማሽነሪዎችን ተረከበ

100

ባህር ዳር ህዳር 29/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የግብርና ቢሮ 298 ሚሊየን ብር ወጭ ተደረጎባቸው የተገዙ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችና ማሽነሪዎችን ተረከበ።

ቢሮው የግብርና መሳሪያዎችና ማሽነሪዎችን የተረከበው ከአምባሰል ንግድ ስራዎች ድርጅት ነው።

ከግብርና መሳሪያዎቹና ማሽነሪዎቹ መካከል 37 የእርሻ ትራክተሮች፣ 29 ሁለገብና አራት የበቆሎ መፈልፈያዎች፣ ሁለት ኮምባይነሮች ጨምሮ የዘር መዝሪያዎችና የኬሚካል መርጫዎች ይገኙበታል።

የአምባሰል ንግድ ስራዎች ድርጅት መካኒካል ኢንጅነር ሄኖክ ሰሎሞን በወቅቱ እንዳሉት ማሽነሪዎቹ የክልሉን ግብርና ለማዘመን የሚያስችሉ ናቸው።

ከአገሪቱ የአየር ንብረትና ስነ-ምህዳር ጋር ተስማሚ በመሆናቸውም ለብዙ ጊዜ ለአርሶ አደሩ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መሆኑን አመላክተዋል።

"መሳሪያዎቹና ማሽነሪዎቹ በመኸርና በመስኖ ልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያስችላሉ" ያሉት ደግሞ በክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ፋይናንስ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ ናቸው።

ዘርፉን ከማዘመን ባሻገር የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብና ድካሙን በመቀነስ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም