ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድንጋጌዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ

123

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015  ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድንጋጌዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ለማስቻል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ቀን ''ሁሉም የሰው ልጆች በነጻነት፣ በእኩልነትና በክብር የመኖር መብት  አላቸው ''በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ይገኛል።

እለቱን ፍትህ ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች እና የፌዴራል ፍርድ በጋራ  አክብረውታል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን አረዳን ጨምሮ የፍትህ ተቋማት ተወካዮችና የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን አረዳ፤  ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድንጋጌዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ለማስቻል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሚያስችል ህግ ተደንግጎ እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የአገሪቱ ሕግ ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር በማጣጣም ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርና አጠቃላይ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም