የ24ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ሕብረት ስብሰባ እየተካሄደ ነው

108

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 የ24ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ስብሰባ በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

ባለፉት ቀናት በኢትዮጵያ ሲካሄድ ከቆየው ስብሰባ የሚገኘው ግብዓት ለቀጣናው ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተጠቁሟል።

ስብሰባው በቆይታው በሽብር ወንጀል፣ በህገ-ወጥ ስዎችና ጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በአደንዛዥ ዕጽ እና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዙሪያ ሲመክር እንደነበር ተገልጿል።

በዛሬው ዕለትም ኢትዮጵያ የሕብረቱን መሪነት በዕጩነት የምትረከብ ሲሆን ለቀጣይ አንድ ዓመት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተረክበው እንደሚመሩት ይጠበቃል።

በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፣ የቀጣናው የኢንተርፖል ሃላፊዎች፣ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የፖሊስ ተቋማት አዛዦች እና አታሼዎች ተገኝተዋል።

23ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ሕብረት ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ/ኪንሻሳ መካሄዱ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያም ጉባኤውን ስታስተናግድ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም ተመላክቷል።

ተቀማጭነቱን በናይሮቢ/ኬኒያ ያደረገው ሕብረቱ በምስራቅ አፍሪካ አገራት የሕግ አስከባሪ ተቋማትን ትብብር ለማጠናከር፣ መረጃ ልውውጥ ለማጎልበት፣ የጋራ ስትራቲጂ ለመንደፍ እና በቀጣናው ሰላም ለማስፈን በተለይም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመመከት ግብ ይዞ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1998 በኡጋንዳ ካምፓላ መቋቋሙ ይታወሳል።

14 አገራትን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን አባላቱም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሲሸልስ፣ ሩዋንዳ፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኮሞሮስና ቡሩንዲ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም