የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ በምጣኔ ሃብት እድገት ላይ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

150

በሩብ ዓመቱ በወጪና ገቢ የጭነት አገልግሎት ከእቅዱ በላይ ማሳካቱን ገልጿል።

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ470 ሺህ ቶን በላይ የወጪ እና ገቢ ጭነት በማጓጓዝ ከእቅዱ በላይ ማሳካቱን አስታወቀ።

የማህበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ የተቋሙን የሩብ ዓመት ክንውን እና አጠቃላይ የባቡር ትራንስፖርት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ፋይዳ በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ለኢኮኖሚው ከተሰጡት የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር በ19 የባቡር ጣቢያዎቹ የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ በምጣኔ ሃብት እድገት ላይ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የምግብ ዘይት፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን ጨምሮ በድምሩ 471 ሺህ ቶን ጭነት ማጓጓዙን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከእቅዱ በላይ 104 በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልፀው በአገራዊ የወጭና ገቢ ጭነት ሚና ከነበረው የ12 በመቶ ድርሻ ወደ 15 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

በባለፈው በጀት ዓመት በቡና ምርት የወጭ ንግድ 98 በመቶ የሚሆነው የተጓጓዘው በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከ60 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እና የአፈር ማዳበሪያን በማጓጓዝ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ማሳለጥ ተችሏል ነው ያሉት።

በዚህም በሎጂስቲክስ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት በኩል ማግኘት የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ከህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ በቱሪዝም ዘርፍም በኢትዮጵያና ጅቡቲ ጭምር የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም