መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት ይሰራል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

118

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015  መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሰላምና ብልጽግናን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን የአፍሪካውያን ኩራት ለማድረግ እንሰራለን ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን "ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም" በሚል መሪ ቃል  በሐዋሳ በተከበረበት ወቅት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን በማሳካትም የአፍሪካ የሰላም ተምሳሌት ለመሆን ሁላችንም በአንድነት ልንቆም ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የከፍታና የብልፅግና ጎዳና ላይ መሆኗን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በሂደቱ የሚገጥሙን ፈተናዎች ተስፋ ሊያስቆርጡን አይገባም ብለዋል፡፡

ለግጭትና ለውድመት የሚያሴሩ ኃይሎች አርፈው እንደማይቀመጡ በመገንዘብ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በትጋት መስራት አለብን ነው ያሉት።

ያጋጠሙንን ፈተናዎች ለትጋትና ለጥንካሬ በመጠቀም የኢትዮጵያን ልዕልና የሚያረጋገጡ አዳዲስ ድሎችን ለማስመዝገብ ቆርጦ መነሳት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃላፊነት መሆኑን በአፅንኦት ጠቅሰዋል።

ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ማፍረስ ቀርቶ ሊነቀንቋት እንደማይችሉ ሊገነዘቡ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያውያንን በትናንሽ አጀንዳዎች ለመከፋፈል የሚሞከረው ሴራም መክሸፉን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ያላት በአዲስ ትውልድ በይቅርታና በመደመር የፀናች በመሆኗም የሴራ አጀንዳቸውን አክሽፍነዋል፤ በቀጣይም ቢሞክሩ እንደማይሳካላቸው በተግባር እናሳያቸዋለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የጠላቶቿን ሴራና ተንኮል በመበጣጠስ ብልጽግናዋን እንደምታረጋግጥና ታላቅነቷን እንደምታስመሰክር አረጋግጠዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ የሁሉም አፍሪካ መናኸሪያና መዳረሻቸው እንዱሁም ኩራታቸው እስከምትሆን ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የአፍሪካ እምብርት የሆነችዋን ጠንካራዋንና ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስረከብ ሁሉም በአንድነት መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርም የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን የኢትዮጵያውያንን አንድነት በሚገልፅ ደማቅ ዝግጅት በማስተናገዳቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም