የሩሲያ ኤምባሲ የተለያዩ መፃሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መፃሕፍት አበረከተ

135

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ የተለያየ ይዘት ያላቸውን መጽሐፍት ለአብርሆት ቤተመጽሐፍት አበረከተ።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቪግኒ ተርዮክኢን ጨምሮ ሌሎች የኤምባሲው ተወካዮች በተገኙበት መፃሕፍቶቹ ለአብርሆት ቤተ መፃሕፍት ተበርክተዋል።

የተበረከቱት መጽሃፍት በሩሲያ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰቡ መሆናቸው ተገልጿል።

አምባሳደሩ በሁለገቡ የአብርሆት ቤተ መፃሕፍት ባደረጉት ጉብኝት ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸውን መፅሃፍትን በማስረከባቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ለሁሉም ጉዳዮች ቁልፍ መሳሪያ ለሆነው ትምህርት ትኩረት በመስጠት አንባቢ ትውልድ መገንባት ወሳኝ መሆኑንና በተለይም አብርሆት ቤተ-መፃሕፍት የልጆች ማንበቢያ ክፍል መኖሩ ታዳጊዎች መጽሐፍትን እንዲያገላብጡ፣ የዕይታ አድማሳቸው እንዲሰፋና ዓለምን እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

በእለቱ የቤተ-መፃሕፍቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ዉብአየሁ ማሞ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው መፀሐፍቶቹን ተረክበዋል።

በተጨማሪም ዳይሬክተሩ ምክንያታዊና መረጃ ያለው ትውልድ ለመገንባት ሀገር በቀል መፃህፍቶችን ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ያሉ አለም አቀፍ ይዘት ያላቸዉ መፃሕፍት ያሰፈልጋሉ ማለታቸውን ከቤተ-መጽሐፍቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም