የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት ሐላፊ የኢትዮጵያን የበረራ ደኅንነት አጠባበቅ አደነቁ

139

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 28 ቀን 2015 የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት ሐላፊ የኢትዮጵያን የበረራ ደኅንነት አጠባበቅ አደነቁ።

የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ረዳት ሐላፊ ካሪግ ሊየንስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ደይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ ከበረራ ደኅንነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጠው አገልግሎት በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ስም ያለው መሆኑን በምክክሩ ወቅት ያነሱት የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ረዳት ሐላፊ ይህ ውጤት በበረራ ደኅንነት ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎችና የተገነቡ አቅሞች ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከበረራ ደኅንት ጋር በተያያዘ በሰው ኃይል፤ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት ጠንካራ መሰረት መጣሉን እንደተገነዘቡ ገልጸው አሜሪካ የበረራ ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ በቴክኒክ፣ በሎጀስቲክስ፣ በቴክኖሎጂና በሥልጠና መስኮች ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍና በጋራ የሚሠሩ ሥራዎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅሰዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ ውስብስብ የደኅንነት ሥጋቶች በተደቀኑበት የአቪዬሽን ዘርፍ ውጤታማ ለመሆንና የኢትዮጵያን አየር መንገድ መልካም ስም ለማስቀጠል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የበረራ ደኅንነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች የማሟላት፤ የሰው ኃይል አቅም የመገንባትና የአደረጃጀት ክለሳዎችን የማከናወን ሰፋፊ ተግባራት መከናወናቸውን የጠቀሱት አቶ ሲሳይ፤ በዚህም ሥጋቶችን ለመቀነስ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ረዳት ሐላፊ ካሪግ ሊየንስ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱን ዲጂታል ኤግዚቢሽን መጎብኘታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም