በመኸር ወቅት በ13 ሺህ 711 ሄክታር መሬት ላይ ለለማ ሰብል የዘር ጥራት ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል-ባለስልጣኑ

195

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 28/2015 በአማራ ክልል በመኽር ወቅት በተለያዩ የሰብል ምርጥ ዘሮች በ13 ሺህ 711 ሄክታር መሬት ላይ ለለማ ሰብል የጥራት ክትትልና ቁጥጥር ስራ ማከናወኑን የክልሉ የግብርና ጥራትና ደህንነት ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ሃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የሰብል ዘር እንዲቀርብ እየተሰራ ነው።

በክልሉ በ2014/15 ምርት ዘመን መኸር ወቅት በተለያዩ የሰብል ምርጥ ዘሮች በ13 ሽህ 711 ሄክታር መሬት ላይ ለለማ ሰብል የዘር ጥራት ክትትልና ቁጥጥር መደረጉን ተናግረዋል።

በተረደረገው የቁጥጥርና ክትትል ስራ በ370 ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል ደረጃውን አሟልቶ ባለመገኘቱ ከዘር ውጭ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

በቀሪው መሬት ላይ የለማ ሰብል ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰበሰብ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የጥራት ደረጃውን ጠብቆ ከለማው ሰብል 334 ሺህ 884 ኩንታል የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የአኩሪ አተርና ምርጥ ዘር ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

የሚሰበሰበው ምርጥ ዘር ለቀጣይ የምርት ወቅት ለአርሶ አደሩ የሚቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርጥ ዘር ልማቱ 12 ሺህ 900 አርሶ አደሮችና 46 የዘር አባዥ ድርጅቶች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት የለማ 210 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ቀርቦ ጥቅም ላይ መዋሉን ሀላፊው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም