የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳካት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ይገባል-ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

119

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 28/2015 የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳካት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና በቅንጅት መስራትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አመለከቱ።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች፣ የታዩ ችግሮች እንዲሁም ቀጣይ መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በግብርና ሚኒስቴር፣ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በጥምረት ባዘጋጁት ጉባኤ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳነት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴንና ሌሎች የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከተረጅነት ለመውጣት በምግብ ራስን መቻል ወሳኝ ሚና አለው።

"ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ መሬት ውስጥ ለእርሻ ጥቅም ላይ የዋለው 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የሚታረሰውን መሬት በማስፋት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ማጠናከር ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል።

ለዚህም ዘመናዊ እርሻን በመተግበርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።     

መንግስት በሌማት ትሩፋት የተለያዩ የምርት ዓይነቶችንና ጥራትን ለማሳደግ የጀመረው እንቅስቃሴ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙና ሀገር ገንቢ ትውልድ ለማፍራት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።   

ያለንበት ጊዜ የውድድር መሆኑን በማንሳት ኋላቀር አስተራረስንና የአመራረት ባህልን በመቀየር ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር አብሮ የሚጓዝ ኢኮኖሚ እንድትገነባ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

ከቴክኖሎጂ ባሻገር የአርሶ አደሮች፣ የማህበራት የመንግስትና የግል ተቋማት ቅንጅት ለምርታማነት ማደግ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።   

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጫና ለመቋቋም አረንጓዴ አሻራ ላይ በስፋት እየሰራች መሆኑን አውስተው፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው የግብርናው ዘርፍ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት /ጂ ዲ ፒ/ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።     

ለአብነትም የስንዴ፣ የቡና፣ የአኩሪ አተር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው በወተት፣ በስጋ፣ በዶሮ፣ በማርና በሌሎች ምርቶች ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።

በተለይም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በበጋ ስንዴ ልማት ሀገሪቱ  ከተረጂነት እንድትላቀቅ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።   

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ እጥረት ትልቁ ችግር መሆኑን ጠቁመው ችግሩን በፖሊሲ ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋለ።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም