የጤና ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የድንገተኛ ሕክምና ምላሽ እና ጤና ተቋማትን አገልግሎት የማስጀመር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ

79

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 28 2015 በትግራይ ክልል የድንገተኛ ሕክምና ምላሽ እና ጤና ተቋማትን አገልግሎት የማስጀመር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የሕክምና አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሰብአዊ እርዳታ፣ የሕይወት አድን ሕክምና የስርዓተ ምግብ እንዲሁም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ስራ በሚኒስቴሩና አጋር ድርጅቶች እየተከናወነ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

መድሃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶችን ማድረስ በተመለከተ:

ከጎንደር መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ወደ ሽሬ ቅርንጫፍ በተለያዩ ዙሮች በተደረገ ጭነት 13 ሚሊዮን 460 ሺህ 305 ብር የሚያወጣ የሕይወት አድን መድኃኒቶችና የሕክምና ግብቶችን ሽሬና አቅራቢያው የሚገኙ ከተሞች ማድረስ ስለመቻሉ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ከደሴ ቅርንጫፍ ወደ አለማጣ እና በአካባቢዉ ላሉ ጤና ተቋማት ብር 20 ሚሊዮን 434 ሺህ 489 ብር የሚያወጡ የሕይወት አድን መድኃኒቶችና የሕክምና ግብአቶችን ማድረስ ተችሏል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

የጸረ-ወባ፣ የስኳር፣ የኩላሊት እጥበት (dialysis)፣ ፀረ-ቲቢ፣ ጸረ-ደም ግፊት፣ የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የሚውሉ እና ሌሎች የህይወት አድን መድኃኒቶች ግምታቸው ብር 78 ሚሊዮን 763 ሺህ 353 ብር የሚያወጡ በዓለም ጤና ድርጅት እና በባለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል ወደ መቀሌ ማድረስ እንደተቻለ አስታወቋል።

በአጋር ድርጅቶች በኩል በተለያዩ ዙሮች 158.3 ሜትሪክ ቶን የሚመዝን የህይወት አድን መድኃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ወደ መቀሌ እና በዙሪያዉ ላሉ ጤና ተቋማት ማድረስ የተቻለ ሲሆን ተጨማሪ የሕይወት አድን ህክምና ግብዓቶችን ለማድረስ በሂደት ላይ እንደሚገኝም አመልክቷለ፡፡

የመቀሌ እና የሽሬ ቅርንጫፎች በተገቢው መንገድ የሕይወት አድን መድሃኒቶች እና የህክምና ግብዓቶችን እየተቀበሉና እያሰራጩ ይገኛሉ ነው ያለው ሚኒስቴሩ ብሏል።

የጤና አገልግሎት ትግበራን በተመለከተም:

የሕክምና አገልግሎት ለማስጀመር እና የመስክ ምልከታ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴርና ከተለያዩ ሆስፒታሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች ወደ ሽሬ፣ አክሱም እና አድዋ ከተሞች ተልከዋል ብሏል፡፡

ሽሬ፣ አክሱም እና አድዋ ሆስፒታል እና በአቅረቢያው ባሉ ጤና ጣቢያዎች የመስክ ምልከታ ተደርጎል፡፡ በሽሬ ስሁል ሆስፒታል ከጦርነቱ በፊት ከነበሩ 520 ሰራተኞች ውስጥ 411 ወደ ስራ ለመመለስ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ሆስፒታሎቹ የተመላላሽ፣ ተኝቶ ማከሚያ፣የድንገተኛ፣ እንዲሁም የላብራቶሪ እና ፋርማሲ የነበሩ እና የተላኩትን ግብአቶች ተጠቅመው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጿል፡፡

ጤና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር እና በሰው ሀይል ለማደራጀት እንዲቻል በሶስት ሆስፒታሎች ማለትም በሽሬ፣ በአክሱም እና በአድዋ እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ 15 ጤና ጣቢያዎች ላይ ወደ ስራ ለተመለሱ ባለሙያዎች ክፍያ የሚውል 3 ሚሊዮን 524 ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረስ በቦታዉ ላይ የፋይናንስ እና የሰው ሀብት ባለሙያዎች የተላኩ ሲሆን በሽሬ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ክፍያው መከፈል መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር አመልክቷል።

በግጭቱ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ የማደራጀት ተግባር ተጠናክሮ አንደሚቀጥል ሚኒስቴሩ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ አሰታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም