በክልሉ የሌብነት ተግባርን በቁርጠኝነት ለመታገል ትኩረት ተሰጥቷል- የሶማሌ ክልል

123

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ህዳር 28 ቀን 2015 የሶማሌ ክልል መንግስት ሙስናና የሌብነት ተግባርን በቁርጠኝነት ለመታገል ትኩረት መስጠቱን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ተወካይ አቶ አህመድ ያሲን ገለጹ።

“ሙስናን በተግባር መታገል!'' በሚል መሪ ሀሳብ የፀረ-ሙስና ቀን ዛሬ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።

የርዕሰ መስተዳድሩ ተወካይና የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ያሲን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ሙስና ህብረተሰቡን ከድህነት ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት ስለሚጎዳ ለመከላከል ህዝቡን ማስተማር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው።

የክልሉ መንግሥት ሙስናንና የሌብነት ተግባርን በቁርጠኝነት ለመታገል ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

የፀረ ሙስና ቀን ዛሬ በክልል ደረጃ በጅግጅጋ ከተማ መከበሩ በክልሉ በህዝብና በመንግስት ሀብት ላይ የሚፈፀመው ስርቆት በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት የጋራ ቅንጅት እንዲፈጥሩ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡   

የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብዲወሊ ጃማዕ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከሙስና ጋር በተያያዘ ከቀረቡለት 97 ጥቆማዎች 51  ክስ እንዲመሰረትባቸው ለፍትህ ቢሮ መተላለፋቸውን አስታውቀዋል።

ሙስናን የሚፀየፍ ስነ-ምግባር ያለው ትውልድ ለመገንባት የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደጉ በተጓዳኝ ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት በሴክተር ቢሮዎች የስነ ምግባር መከታተያ ባለሙያዎች ለማደራጀት በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ተወካይ ሼህ አህመድ ሼህ ዑመር፤ ሙስናን በመከላከል ዜጎች በጥረታቸው ብቻ እንዲያድጉ ህዝቡን በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የሶማሌ ክልል ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪ መልአከ መዊዕ ቆሞስ አባ ጽጌ ደስታ በበኩላቸው፤ "ሌብነትን የሚፀየፍ መልካም ትውልድ ለመፍጠር ህዝቡን በማስተማር የእምነት አባቶች የቤት ስራ መሆን አለበት" ብለዋል።

በበዓሉ ላይ  የክልሉ አመራሮች፣  የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም