የንግድ ማህበረሰብ አባላትን ግንዛቤ በማሳገድ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እሰራለሁ ...የደብረብርሃን ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት

74
ደብረብርሀን መስከረም 18/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በወጪና ገቢ ንግድ ሥራ የተሰማሩ የንግድ ማህበረሰብ አባላትን ግንዛቤ በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እንደሚሰራ የደብረብርሃን ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ። የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ታምሩ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት አንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አቅም እያላቸው ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ በወጪ ንግድ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም በተያዘው ዓመት የግንዛቤ ችግሩን ለመፍታት በመረጃ ልውውጥ፣ በሒሳብ መዝገብ አያያዝ፣ በገበያ ማፈላለግና መጠቀም ላይ ያተኮረ ተከታታይ የክህሎት ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን አመለክተዋል። ለስልጠናው ዝግጅት መደረጉን የገለጹት አቶ ታምሩ ስልጠናው በነጋዴዎች መካከል የሚኖረውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተትን በመለየት በደረጃቸው ለውጥ የሚያመጣ እንደሚሆን አመልክተዋል። በስልጠናው 150 በወጭና ገቢ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ለማሰልጠን መታቀዱንና ለእዚህም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። "ነጋዴዎችን ከመደበኛ ስልጠናው ባሻገር በአጫጭር ስልጠናዎች ግንዛቤያቸው እንዲያድግ መደረጉ አቅማቸውን ለማሳደግና በሚያቀርቡት ምርት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል" ብለዋል። ደብረ ብርሀን ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የምትገኝ በመሆኑ በቱሪዝም፣ በአምራችና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮዽያ ንግድ ባንክ  የደብረ ብርሃን ሥራ አስኪጅ አቶ ብርሃኑ ምትኩ በበኩላቸው በውጪ ንግድና በግብርና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚሳተፉ ባለሀብቶች የባንኩን መስፈርቶች አሟልተው ከመጡ ብድር እንደሚያገኙ ተናግረዋል። እስካሁንም ወደራ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩንዬን ጨምሮ ሁለት ድርጅቶች ከባንኩ ባገኙት የገንዘብ ብድር በወጪ ንግድ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ሚስጥረ በቀለ ለነጋዴ ሴቶች ቀደም ሲል በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ  ሲሰጣቸው የነበረ ሙያዊ ስልጠና ሴት ነጋዴዎች እንዲበቁ ማገዙን ገልጸዋል። በእዚህም ነጋዴ ሴቶች ጥራቱን የጠብቀ ምርት ማምረት በመጀመራቸው የገቢ ምንጫቸው እያደገ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር ተባብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። የደብረ ብርሃን ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከ6 ሺህ በላይ አባል ነጋዴዎች ያሉት ሲሆን 1 ሺህ 20 አዲስ አባል ለማፍራት ግብ አቅዶ እየሰራም ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም