በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ በጋ ወራት 6 ሺህ 448 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናል - ቢሮው

145

ሀረር (ኢዜአ) ህዳር 28 ቀን 2015  በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ በጋ ወራት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት የሚሸፍን 6 ሺህ 448 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እንደሚከናወን የክልሉ ግብርና ቢሮ አመለከተ።

ቢሮው በክልሉ ለሚገኙ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለሞያዎች በተፋሰስ ልማት ላይ ያተኮረ ስልጠና ዛሬ መስጠት ጀምሯል።

በስልጠናው መክፈቻ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር የተፋሰስ ልማት ስራዎች ጉልህ አስተዋጽዎ ማበርከታቸውን አብራርተዋል።

የመሬት ምርታማነት አቅምን ይበልጥ ለማጎልበት የተፋሰስ ልማት ስራ ወሳኝ በመሆኑ የተጀመሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ምግብ ዋስትና አስተባባሪ አቶ ኤልያስ ከዲር በበኩላቸው "በክልሉ በዘንድሮ በጋ ወራት 6 ሺህ 448 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናል"

በዚህም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ይከናወናል ነው ያሉት።

በተፋሰስ ልማት ስራው ላይ 8  ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሳተፉ አቶ ኤሊያስ አያይዘው ተናግረዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ 18 ቀናት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው በዚሁ በመጀመሪያ ዙር የባለሙያዎች ስልጠና ላይ ከክልሉ 7 ዞኖች የተውጣጡ 755 የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም