የመቀሌ የኤሌክትሪክ ሃይል መስመር ከብሔራዊ የሃይል ቋት ጋር ተገናኘ

587

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27 /2015 በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ከዓመት በላይ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር ተቋርጦ የቆየው የመቀሌ ከተማ ከብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል(ግሪድ) ጋር ተገናኝቷል መገናኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት መስመሩ ከብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ጋር የተገናኘው ከአላማጣ መሆኒ በተዘረጋው የባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ከተጠናቀቀ በኋላ ነው።

በመስመሩ ፍተሻና የጥገና ሥራ ላይ በሰሜን ምስራቅ ሪጅን አስተባባሪነት ከሁሉም ሪጅን የተውጣጡ የማከፋፈያ ጣቢያና ማስተላለፊያ መስመር የጥገና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የመስመሩ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት መጀመር በትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ መልሶ ሥራ ለማስጀመር የተጀመረውን ሥራ የሚያፋጥነው ይሆናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁመራ እስከ ሽሬ ድረስ የተዘረጋው የባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ተጠናቋል።

ይሁንና ለሽሬ ኃይል የሚሰጠው ከተከዜ እስከ አክሱም በተዘረጋው መስመር ስምንት ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማጋጠሙ ጥገናው ወደ ተከዜ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ቀጥሏል።