ኢትዮጵያ ያለማቻቸው የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል

123

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27 ቀን 2015  ኢትዮጵያ የራሷን ማህበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም ያለማችውን መተግበሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ተሳትፎ እንዲያደርግ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ጥሪ አቀረበ።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የራሷን ማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም የሚያስችሏት መተግበሪያዎች አልምታለች።

ከለሙ መተግበሪያዎች መካከል "ኤርጋ" የተሰኘና የኢሜል ትስስርን የሚተካ፣ "ስርኩን" ዋትስአፕና ቴሌግራምን የሚተካ፣  እንዲሁም "ደቦ" የተሰኘ  የቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚተካ መተግበሪያዎችን ለአብነት አንስተዋል፡፡

መተግበሪያዎቹን ለበርካታ ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ ደግሞ የሚያስችሉ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።

የመሰረተ-ልማት ግንባታዎችን በተቋሙ በጀት ብቻ ማከናወን እንደማይቻል ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ  የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ተሳትፎ እንዲያደርግ  ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ አኳያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች የመተግበሪያ መሰረተ-ልማትን እንደ አንድ አማራጭ መውሰድ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

አንድ አገር የራሷን መተግበሪያ መጠቀሟ ከመላው ዓለም በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሐሰተኛና የተሳሳቱ መረጃዎችን፣ የግል ደኅንነትን ከመጠበቅ አንጻር ጠቀሜታ እንዳለው ይነገራል።

በዓለም ላይ የራሳቸውን ማህበራዊ ሚዲያ አልምተው ለመረጃ ልውውጥ ከሚጠቀሙ አገራት መካከል ቻይና በአብነት ትጠቀሳለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም