ምሁራን ችግሮች ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲፈቱ የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ ይገባል

127

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27ቀን 2015 ምሁራን በሕብረተሰቡ ዘንድ ያሉ ችግሮች ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ በዘላቂነት እንዲፈቱ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስገነዘቡ፡፡

በተጨማሪ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የዴሞክራሲና ሰላም ግንባታ ሂደቶችን በጥናትና ምርምር ማገዝ እንደሚጠበቅባቸውም ነው ጥሪ የቀረበው፡፡

ሀገር አቀፍ የምሁራን የምክክር መድረክ "ለኢትዮጵያ ልዕልና የምሁራን ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ያሉ ያደሩ ችግሮችን መለስ ብሎ ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ምሁራን በሀገሪቱ ሥር የሰደዱ ችግሮችን ከነመፍትሔዎቻቸው በማጥናት በሀሳብ ሊደግፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ምሁራን ሙስናን ለማስፋፋት ግጭትን የሚያቀጣጥል እንዲሁም  ግጭትን በመጠቀም ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መኖራቸውን ተገንዝበው  መንግሥትን ሊያግዙ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከገጠማት ድህነት ተላቃ ወደ ከፍታ እንድትጓዝ አገራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

በመድረኩ የመወያያ ሃሳብ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ዶክተር ደቻሳ አበበ፤  በሁሉም ዘመናት ምሁራን የራሳቸው የሆነ ሀገራዊ አበርክቶ ቢኖራቸውም ከጊዜ ወደጊዜ ግን ሚናቸው እየተዳከመ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ምሁራን የበዳይና ተበዳይ የታሪክ ትንተና ላይ ትኩረት አድርገው ጊዜያቸውን የሚያጠፉ መሆናቸውን ተችተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችም ሀገር ከሚለው ትልቁ ምስል ይልቅ በተግባርና በአሰራር አካባቢያዊ እና ወገንተኝነት የሚስተዋልባቸው እየሆኑ መጥተዋል ነው ያሉት፡፡

ምሁራኑ ኢትዮጵያ ከግጭት እንድትወጣና ግጭቶች እንዳይከሰቱ ከመከላከል አንጻር ሚናቸው ደካማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ኢትዮጵያን በሰላምና መረጋጋት ውስጥ ከፍ ለማድረግ ወደ ኋላ ከሚጎትት አካሄዶች ራሳቸውን በማቀብ ለኢትዮጵያ መሻሻል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ ምሁራን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ምሁራን ከህብረት ይልቅ የልዩነት አስተሳሰብን በማቀንቀን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ከመሆን ይልቅ አባባሽ ሆነናል ብለዋል።

ከብሔር አጥር በመውጣት፣ ትርክቶቻችንን በመቀየር ስለ አብሮነት፣ ስለ ሰላምና ዴሞክራሲ ማጥናት መመራመርና ሥር የሰደዱ ችግሮችን መቅረፍ አለብን ነው ያሉት።

ሰላም የሀገር ግንባታ መሰረት ነው ያሉት ምሁራኑ፤ በዚህ ሂደት የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ሕግ አክባሪነትን በማስፈን ሂደት በጥናትና ምርምር ማገዝ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተለይም ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ መወሰኑ እንዲሁም የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት በዘላቂነት ለማቆም የሰላም ስምምነት መደረጉን ተከትሎ የኢትዮጵያን ሰላም ዘላቂ በማድረግ ሂደት ምሁራኑ ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸው ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም