ሱሰኝነትና የወጣቶች የአምራችነት ጊዜ ፈተና

299

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27 ቀን 2015 ጥናቶች እንደሚያመለክቱት  ሱስ ማለት ተደጋግሞ እንዲወሰድ የሚገፋፋ መጥፎ ልማድ ወይም  በሰዎች ላይ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ የጥገኝነት ስሜት በመፍጠር ለማንቃት፣ ድብርትን ለማስወገድ፣ ጀብድ ለመሥራትና ጊዜን ለማሳለፍ  ብለው የሚጠቀሙት ነው።

ሕመምን ለማስታገስ፣ ከፍተኛ የደስታን ስሜት ለመጎናጸፍ በሚል ምክንያት የሚወሰድና  ጤናማ  የአኗኗርን መንገድ የሚገድብ እንደሆነና ለሱስ ተጋላጭ ከሆነው የሕብረተሰብ ክፍል አብዛኛው ወጣት እንደሆነ ይነገራል።

በአዲስ ሕይወት ሱስ ማገገሚያ ማዕከል ያገኘነው ወጣት ዮሐንስ ግርማ በ20 ዎቹ እድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኝ ሲሆን ገና በ16 ዓመቱ ለመዝናናት በሚል የጫት፣ ሲጋራና አልኮል መጠጦችን እንደጀመረ ያስታውሳል፡፡

ውሎ ሲያድር እንደቀልድ የጀመራቸውን ድርጊቶች በቀላሉ ለመላቀቅ ሳይችል  ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ከቤተሰባዊ ግንኙነቱ የነጠሉት  እነዚህ ድርጊቶቹ ቀስ በቀስ በማህበራዊ ህይወቱ ላይ ፈተና እንደደቀኑበትም ይናገራል።

በሱስ ሳቢያ ያጋጠመው ማህበራዊ ችግር እየተደጋገመና እየጨመረ በመምጣቱ ከሰዎች ተነጥሎ የሱስ ታማሚ ለመሆን እንደተዳረገ አንስቶ ሰርቼ ቤተሰቦቼንና አገሬን በምጠቅምበት የወጣትነት  ጊዜዬን በሱስ አባከንኩት ይላል።

በማገገሚያው ያገኘነው ሌላኛው ወጣት ኤርሚያስ መርጋ "ሕይወትህን የምትገዛው በራስህ አዕምሮ ሳይሆን በምትጠቀምባቸው ነገሮች ግፊት ከሆነ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ይኖርብሃል" ብሏል።

ላለፉት አሥር ዓመታት በሱስ ተይዞ ከማህበራዊ ሕይወቱ በመገለል እንደቆየና ለነገ ስፊ ራዕይ የሚሰነቅበትን ጊዜ በሱስ ምክንያት እንዳባከነው ነው የገለጸው።

የጫት፣ ሲጋራና መጠጥ ሱስ የጀመረው ገና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ኤርሚያስ "እንደቀላል ትጀምረውና ለመውጣት አበሳህን የምታይበት ነው" ይላል።

ሱሰኛ የሆነው በጫት በመጠጥና ሲጋራ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ኤርሚያስ የመጀመሪያ ጊዜያት ደስተኛ ያደርግህና በኃላ ላይ  በማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ  ተጎጂ ያደርግሃል ነው ያለው፡፡

በማገገሚያ ማዕከሉ ያገኘናቸው ወጣቶች ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ከሱስ እንዳገገሙ ተናግረው 'ወደ ሱስ ለማግባት ቀላል እንደሆነ ሁሉ ከህመሙ ለማገገም  ቀላል አይደለም ብለዋል።

በአዲስ ሕይወት ሱስ ማገገሚያ ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ይርገዱ በሀብቱ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት አደጋ ውስጥ የጣለ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራበት የሚገባ ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከጫት ጀምሮ የአልኮል መጠጦችና የተለያዩ ሱስ አስያዥ መድኃኒቶች ጭምር የሚጠቀሙ ወጣቶች በስፋት መኖራቸውን ያወሳሉ፡፡

መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡም ልጆቹ በሱስ እንዳይጠመዱ የቅርብ ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ የሚናገሩት ሲስተር ይርገዱ ሱስ እየተባባሰ ከሄደ ለአዕምሮ ሕመም መንስኤ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስነ-አዕምሮ ስፔሻሊስት ዘገየ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ሱሰኝነት እየጨመረ ከመጣ ለዘላቂ የአዕምሮ ጤና ችግር ሊዳርግ እንደሚችል ነው የሚናገሩት፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት በርካታ ወጣቶች በጫት፣ በአልኮልና በሺሻ በመሳሰሉ ሱስ አስያዥ ነገሮች እየተጠቁ ወደ ሕክምና ተቋም መምጣታቸውን ጠቁመው እነዚህን ነገሮች ለመቆጣጠር የወጡ አንዳንድ ሕጎች ቢኖሩም የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

በተለይ ከአልኮልና ከጫት ጋር ተያይዞ በርካታ ታማሚዎች ወደ ሆስፒታሉ እንደሚመጡ የተናገሩት አቶ ዘገየ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት በ2022 ባወጣው ሪፖርት ላይ በዓለማችን ላይ ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለባቸው አስታውቋል።

ይህን መሰረት አድርጎ በተሰላ ቀመርም በሀገራችን 15 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በአዕምሮ ህመም ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት አለ፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም