ምሁራን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራትን በጥናት ሊደግፉ ይገባል

165

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27/2015 ምሁራን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራትን በጥናትና ምርምር ሊደግፉ እንደሚገባ ተጠቆመ።

"ለኢትዮጵያ ልዕልና የምሁራን ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የምሁራን ምክክር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በምክክሩም፤ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ምሁራን ያላቸው አበርክቶ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በኢዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኤስያ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ በዚሁ ጊዜ ምሁራን በሀገር ጉዳይ የሚጠበቅባቸውን ያህል ተሳትፎ እያደረጉ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች በተደቀኑባት ወቅት ምክንያታዊ በሆነ አግባብ በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ ከመሞገት ይልቅ በዝምታ የማለፍ አዝማሚያ እንደተስተዋለባቸው ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ደግሞ  የሀገር መንግስትና የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም መደበላለቅ፣በርዕሰ ጉዳዮች ላይ በቂ ጥናትና ምርምር አለማድረግ እንዲሁም ፍረጃን መፍራት በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ምሁራን ለሀገራቸው ሉዓላዊነት መፅናት ያለማንም ቀስቃሽነት በትጋት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ምሁራን በበኩላቸው በቀደምት ኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት ተከብራ የኖረችውን ኢትዮጵያን በማስቀጠል ረገድ የዚህ ዘመን ምሁራን በሚጠበቅባቸው ልክ አለመስራታቸውን ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ኢትዮጵያ ተከብራ እንድትኖር ከመስራት ይልቅ ለውጭ ኃይልች በር የሚከፍት የክፍፍልና የግጭት አጀንዳዎችን የማስፈጸም ሰለባም መሆናቸውን ነው የጠቀሱት።

በመሆኑም የሀገር ፍቅር ሊኖረን ይገባል ያሉት ምሁራኑ፤ ከዚህ አኳያ ለሀገርና ህዝብ ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተን የመስራት ኃላፊነታችንን በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ያለ ኢኮኖሚ ብልፅግና የኢትዮጵያ ልዕልና ሊረጋገጥ እንደማይችል ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ምሁራን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን የሚያመጡ ጥናትና ምርምሮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በአንድነት ካረጋገጡ ቀደምቶቻችን በመማር በህብረት መቆምና አፍራሽ አስተሳሰብን ማስወገድ አለብን ነው ያሉት፡፡

ምሁራን ለኢትዮጵያ ልዕልና የትምህርት ጥራትና ሀገር ወዳድ ዜጋ መቅረፅ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ያነሱት።

ዜጎች የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲኖራቸውና በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር ምሁራን በጥናትና ምርምር በመታገዝ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም